“እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊያሳዩት የሚገባው ምግባር ይህ ነው”
ከኦሽቪትዝ ተርፎ የወጣው ቲቦር ቮል አርቢት ማክት ቶት—አይነ ዩገንት ኢን ኦሽቪትስ (ሥራ ይገድልሃል—ወጣትነት በኦሽቪትዝ) በተባለው በ1990 ባሳተመው መጽሐፉ ላይ ሁለት እስረኞች እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ የሰማውን በዝርዝር ዘግቧል። አንድ ኦስትሪያዊ እሱ “አማኝ እንዳልሆነ” ተናግሮ ነበር። ይሁን እንጂ የወይን ጠጅ ቀለም ያለውን የሦስት መዓዘን ምልክት (ፐርፕል ትሪያንግል) ያደረጉትን እስረኞች ማለትም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን በማወደስ ተናግሯል። የይሖዋ ምሥክሮች በካምፑ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ነበር።
ይህ ኦስትሪያዊ ለጓደኛው እንዲህ ብሎታል፦ “ወደ ጦርነት አይሄዱም። ማንንም ሰው ከመግደል ይልቅ ራሳቸው ቢገደሉ ይመርጣሉ። በእኔ አመለካከት እውነተኛ ክርስቲያኖች ሊያሳዩት የሚገባው ምግባር ይህ ነው ብዬ አስባለሁ። ከእነሱ ጋር በነበርኩበት ጊዜ ያየሁትን አስደሳች ነገር ላጫውትህ። በስቱትሆፍ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ከአይሁዶችና ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር በአንድ ሕንፃ ውስጥ ነበርኩ። በእነዚያ ጊዜያት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከሕንፃው ውጭ ወጥተው በጣም ኃይለኛ በሆነው ቅዝቃዜ ውስጥ መሥራት ነበረባቸው። በዚያ ቅዝቃዜ እንዴት በሕይወት እንደቆዩ ሊገባን አልቻለም ነበር። ይሖዋ ብርታት ስለሰጠን ነው ይላሉ። በጣም ስለተራቡ የምትሰጣቸውን ዳቦ በጣም ይፈልጓት ነበር። ይሁን እንጂ ምን እንዳደረጉ ታውቃለህ? የተሰጣቸውን ዳቦ በሙሉ አንድ ላይ ከሰበሰቡ በኋላ ግማሹን ወሰዱና የቀረውን ግማሽ ደግሞ ከሌላ ካምፕ ለመጡ በጣም እርቧቸው ለነበሩ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ሰጧቸው። እየሳሙ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉላቸው። ከመብላታቸው በፊት ጸለዩ፤ ከዚያም ፊታቸው በደስታ በራ። ከዚያ በኋላ ማንም አልተራበም አሉ። አየህ፣ ከዚያ በኋላ እኔም ‘እውነተኛ ክርስቲያኖች እነዚህ ናቸው’ ብዬ አሰብኩ። እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆን ይገባቸዋል ብዬ ሁልጊዜም አስብ የነበረው እንደዚህ ነበር። በዚህ በኦሽቪትዝ ለተራቡ ጓዶች እንደዚህ ዓይነት አቀባበል ቢደረግ ኖሮ እንዴት ጥሩ ነበር!”