የአቋም ንጽሕናችሁን ጠብቃችሁ በሕይወት ኑሩ!
“እግዚአብሔርን ስደብና ሙት”! የመጽሔታችን ሽፋን፣ የኢዮብ ሚስት በእነዚህ ቃላት ባሏን ልታጠቃው እንደሞከረች ያሳያል። ይህ የሆነው የዛሬ 3,600 ዓመታት ገደማ ነበር። ቢሆንም ይህ በታማኙ የአምላክ አገልጋይ ላይ የተሰነዘረ የቃላት ትንኮሳ እስከ ዛሬ ድረስ በሰው ዘር ፊት የተጋረጠውን አከራካሪ ጉዳይ ያጎላል። ታማኙ ኢዮብ ከብቱን፣ ቤቱንና አሥር ልጆቹን መና ያስቀረበት ኃይለኛ ጥፋት ደረሶበታል። አሁን ደግሞ ጽናቱን እስከ መጨረሻ በሚፈታተን ሥር የሠደደ በሽታ መላ አካሉ ፍዳውን እያየ ነው። ምክንያቱ ምንድን ነው? የአምላክና የሰው ቀንደኛ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ብርቱ መከራ ቢደርስባቸው ሰዎች ንጹሕ አቋማቸውን ሳያበላሹ ከአምላክ ጋር አይጣበቁም በማለት የጀመረውን ግድድር በተግባር ለማሳየት እየጣረ ስለ ነበር ነው።—ኢዮብ 1:11, 12፤ 2:4, 5, 9, 10
እንደ ኢዮብ ዘመን ሁሉ ዛሬ “ዓለምም በሞላው በክፉው” በሰይጣን ዲያብሎስ ተይዟል። (1 ዮሐንስ 5:19) “ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስ እና ሰይጣን” ከሰማይ ወደ ምድር በተጣለበት በአሁኑ ጊዜ የዚህ እውነታነት ከቀድሞው ላቅ ያለ ነው። (ራእይ 12:9) በጊዜያችን ያለው የሰውን ዘር ቁም ስቅል የሚያሳየው ሐዘን የዚህ ውጤት ነው። በ1914 የፈነዳው አንደኛው የዓለም ጦርነት “የምጥ ጣር መጀመሪያ” ምልክት በመሆን እስካለንበት 20ኛው ዘመን ድረስ ተንሠራፍቶ ቀጥሏል።—ማቴዎስ 24:7, 8
በዚህ ጨካኝ፣ የዘቀጠ ዓለም ውስጥ የሰው ጽናት የሚያከትምበት ደፍ ላይ የደረስክ መስሎ ተሰምቶህ ያውቃልን? ‘ሕይወት ሌላ ዓላማ አለው?’ ብለህስ ተገርመህና ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህ? ኢዮብ እንደዚህ ቢሰማውና አንዳንድ ስህተቶችን ቢሠራም በአምላክ ላይ ያለውን እምነት ግን አልጣለም። ያለውን ቁርጥ ሐሳብ፦ “እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም” በሚሉት ቃላት ገልጿል። ‘አምላክ ፍጹም አቋሙን’ እንደሚያውቅለት በሙሉ ልብ ተማምኗል።—ኢዮብ 27:5፤ 31:6
የአምላክ ልጅ ራሱ እዚህ ምድር ሳለ ጽናትን የሚጠይቁ ፈተናዎች ደርሰውበት ነበር። ሰይጣን በብዙ መንገዶች ተተናኩሎታል። በተራራው ፈተና ላይ የኢየሱስን መራብ የራሱን ግብ ለማሳካት ሊጠቀምበት ሞክሯል፤ እንዲሁም በአምላክ ቃል ላይ ምን ያህል እንደሚመካ ፈትኖታል። (ማቴዎስ 4:1–11) ከሃዲ ጻፎችና ፈሪሳውያን እንዲሁም በእነሱ የተጭበረበሩ ደቀ መዝሙሮቻቸው እንዲያሳድዱት፣ አምላክን ተሳድቧል ብለው እንዲከሱትና ለማስገደል እንዲያሴሩበት በማድረግ የኢየሱስን ልብ አስጨንቋል። (ሉቃስ 5:21፤ ዮሐንስ 5:16–18፤ 10:36–39፤ 11:57) በኢየሱስ ላይ ያደረሱበት መከራ ሦስቱ የውሸት አጽናኞች በኢዮብ ላይ ከፈጸሙበት የከፋ ነበር።—ኢዮብ 16:2፤ 19:1, 2
በጌተሰማኒ የአትክልት ስፍራ ኢየሱስ ወደዚህ የፈተናው ከፍተኛ ደረጃ ቀርቦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ “ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች” ብሎ ነገራቸው። ከዚያም “በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ፦ አባቴ፣ ቢቻልስ፣ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ አንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ።” በመጨረሻም በመከራ እንጨት ላይ ሳለ ኢየሱስ “አምላኬ አምላኬ፣ ስለ ምን ተውኸኝ?” ብሎ በመጮኽ የመዝሙር 22:1ን ትንቢታዊ ቃላት ፈጸመ። ነገር ግን ኢየሱስ ፍጹም አቋም ይዞ ከአባቱ ጋር በመጣበቅ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚከተሉት አርአያ ስለተወላቸው አምላክ እስከ መጨረሻው አልተወውም። ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት በማስነሳትና በሰማየ ሰማያት ውስጥ ከፍ ከፍ እንዲል በማድረግ በንጹሕ አቋም ጠባቂነቱ ክሶታል። (ማቴዎስ 26:38, 39፤ 27:46፤ 2:32–36፤ 5:30፤ 1ጴጥሮስ 2:21) አምላክ ንጹሕ አቋማቸውን ሳይለውጡ ከእርሱ ጋር ለሚጣበቁ ሁሉ እንዲሁ ተገቢውን ወሮታ ይከፍላቸዋል።
የኢየሱስ ንጹሕ አቋም ጠባቂነት ለሰይጣን ግድድር መልስ በመስጠት ብቻ ሳይወሰን ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት በማድረግ ንጹሕ አቋም ጠባቂዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መሠረት የሆነውን ቤዛ አስገኝቷል። (ማቴዎስ 20:28) በመጀመሪያ ኢየሱስ በመንግሥተ ሰማያት ከእርሱ ጋር ወራሽ የሚሆኑትን የተቀቡትን “ታናሽ መንጋ” ሰበሰበ። (ሉቃስ 12:32) በመቀጠል በአምላክ መንግሥት ግዛት ውስጥ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት መውረስ ይችሉ ዘንድ “ከታላቁ መከራ” እንዲተርፉ “እጅግ ብዙ ሰዎች” በመሰብሰብ ላይ ናቸው።—ራእይ 7:9, 14–17
ንጹሕ አቋም ጠባቂው ኢዮብ የዚህ ሰላማዊው “አዲስ ዓለም” ማኅበረሰብ ክፍል ለመሆን ትንሣኤ ከሚያገኙት ቢልዮኖች መካከል አንዱ ይሆናል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ዮሐንስ 5:28, 29) በመጽሔታችን የጀርባ ሽፋን ላይ በሥዕል እንደተገለጸው ይሖዋ ‘ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ስለባረከ’ ንጹሕ አቋም ጠባቂነት በኢዮብ ዘመን ዋጋ ያስገኝ ነበር። ‘በከንፈሩ ያልበደለ’ በመሆን መንፈሳዊ ጥንካሬ አግኝቷል። አምላክ ሕይወቱን በተጨማሪ 140 ዓመታት አራዝሞለታል። በቁሳዊ በኩል ቀድሞ ከነበረው እጥፍ ሰጥቶታል፤ “ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ሆኑለት”። በአገሩ ሁሉ ካሉት ጋር ሲነጻጸር ሴቶች ልጆቹ እጅግ መልከ መልካም ነበሩ። (ኢዮብ 2:10፤ 42:12–17) ነገር ግን ይህ ሁሉ ብልጽግና የአቋም ንጽሕናቸውን የሚጠብቁ ሰዎች ገነት በምትሆነው “አዲስ ምድር” ውስጥ ለሚደሰቱበት በረከት ቅምሻ ብቻ ነው። ቀጣዮቹ ገጾች እንደሚያሳዩት አንተም የዚህ ደስታ ተቋዳሽ ልትሆን ትችላለህ!
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ከንጹሕ አቋሙ ፍንክች ባለማለት ፍጹም ምሳሌ ሆኗል