“እንደ ዛፍ ዕድሜ”
ከሦስት ሺህ ዓመት በፊት ሙሴ “የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፣ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው” በማለት ጽፏል።—መዝሙር 90:10
ምንም እንኳን በሕክምናው መስክ ከፍተኛ መሻሻል ቢደረግም የሰው አማካይ የዕድሜ ርዝመት ሙሴ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ከነበረው የዕድሜ ርዝመት ጋር እኩል ነው። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ እንዲህ ያለ በቅጽበት ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ሕይወት ይዞ ሁልጊዜ አይቀጥልም። አምላክ በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ “የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፣ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና” ብሏል።—ኢሳይያስ 65:22
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በነበሩት አገሮች ውስጥ ረጅም ዕድሜ ከሚኖሩት ዛፎች መካከል አንዱ የወይራ ዛፍ ነው። በሥዕሉ ላይ የሚታየው ዛፍ በገሊላ እስከ አሁን ድረስ ለምልመው ከሚገኙት ብዙ ሺህ ዓመት ዕድሜ ካላቸው የወይራ ዛፎች መካከል አንዱ ነው። የሰው ልጅ ይህን ያህል ረዥም ዕድሜ መኖር የሚችለው መቼ ነው? ይህ የሚሆነው አምላክ በሚፈጥረው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ውስጥ እንደሚሆን ይኸው ትንቢት ይገልጻል።—ኢሳይያስ 65:17
የራእይ መጽሐፍም “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” እንደሚመሠረት ተንብዮአል። ይህም የሚሆነው አምላክ ‘እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ሲያብስ፣ ሞት ወይም ኀዘን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ በማይኖርበት’ በአዲስ ሰማያዊ መስተዳድርና በአዲስ የሰው ዘር ኅብረተሰብ ውስጥ ነው።—ራእይ 21:1, 4
ይህ መለኮታዊ ተስፋ በቅርቡ ይፈጸማል። ከዚያም የወይራ ዛፍ ዕድሜ የ24 ሰዓት ርዝመት እንዳለው እንደ አንድ ቀን የሚታይበት ጊዜ ይመጣል። በእጆቻችን ሥራ ሙሉ በሙሉ የምንደሰትበት በቂ ጊዜ ይኖረናል።