የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ—ዛምቢያ
ዛምቢያ በደቡብ ማዕከላዊ አፍሪካ እምብርት በ1,200 ሜትር ከፍታ ላይ ተንጣልሎ በሚገኝ ሸንተረራማ አምባ ላይ የምትገኝ አገር ናት። በስተ ሰሜን ምሥራቅ በኩል 2,100 ሜትር ከፍታ ያለው የመቺንገ ተራራ ጉብ ብሎ ይታያል። በዓለም ላይ በጣም ወደታወቀው የቪክቶሪያ ፏፏቴ የሚያስገመግመው ሞገደኛው የዛምቤዚ ወንዝ የባሕር በር የሌላትን የዚህችን አገር አብዛኛውን ደቡባዊ ድንበር ያካልላል። ከ70 የሚበልጡ የተለያዩ ጎሳዎችን ያቀፈ ሕዝብ ይገኛል። በዚህች አገር በስፋት የሚነገሩት ቋንቋዎች ስምንት ይሁኑ እንጂ ሌሎች ብዙ ቋንቋዎችም አሉ።
በ1911 አንድ ሌላ ቋንቋ በዛምቢያ ምድር መስፋፋት ጀመረ። ከውጭ የመጡ ጎብኚዎች የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅጂዎች ወደ አገር ውስጥ ካስገቡ ጊዜ ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች በዛምቢያ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሆነውን “ንጹሕ ልሳን” ለማሰራጨት ሲጥሩ ቆይተዋል። (ሶፎንያስ 3:9) ከገጠሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች አንዱ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ የነበረው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ እምነት ነበር። ሰዎች እውነትን መማራቸውና አጉል እምነት እንዴት ባሪያ እንዳደረጋቸው ማወቃቸው ነጻ አውጥቷቸዋል!—ዮሐንስ 8:32
ለምሳሌ ያህል አንዲት እህት እንዲህ ስትል ሪፖርት አድርጋለች፦ “አጎቴ በድንገት ሲሞት በዛምቢያ የሚገኘው የዩናይትድ ቸርች አዘውታሪ አባል የነበረችው እናቴ የምትይዘውን የምትጨብጠውን አጣች። ሳምንት ከሚፈጀው የቀብር ሥርዓት በኋላ እንዴት እንደሆነች ለማወቅ ወደ መንደሩ ተመለስኩ። እዚያ እንደደረስኩ አንድ አረጋዊ ሰው ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ አገኘሁ። ሰውዬው ሲሄድ ማን እንደሆነ አያቴን ጠየቅኋት። እርሷም ጠንቋይ እንደሆነ ነገረችኝ። እናቴ የወንድሟን ሞት እንዲበቀልላት ፈልጋ ነበር። ይህንንም ያደረገችው የወንድሟ ነፍስ እረፍት እንድታገኝ ነው። እንደ እርሷ አባባል በዚያ ወቅት ‘ነፍሱ እንዲሁ እየተቅበዘበዘች’ እንደሆነ አድርጋ ታስብ ነበር።”
“አያቴም ቤተሰቡ ለጠንቋዩ የሚከፍለው ገንዘብ እየፈለገ ስለነበር የእኔ እዚያ መገኘት ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ነገረችኝ። ገንዘብ እንዳዋጣ ጠየቀችኝ፤ ይሁን እንጂ ክርስቲያን እንደመሆኔ መጠን ላዋጣ እንደማልችል በጥበብ ነገርኳት። ሙታን አንዳችም ሊያስቡ እንደማይችሉ የሚያሳየውን መዝሙር 146:4ን አውጥቼ በማወያየት ‘የምትቅበዘበዝ ነፍስ’ እንደሌለች አስረዳኋት። እንዲሁም በቀል የእኛ ሳይሆን የይሖዋ እንደሆነ በሚናገረው በሮሜ 12:19 ጥቅስ ላይ ተወያየን። ከዚያም በኋላ በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ኢየሱስ የሰጠውን የትንሣኤ ተስፋ ለእናቴ ነገርኳት። አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ ባለኝ ጠንካራ እምነት በጣም ተነካች። ወዲያው ከአንዲት ምሥክር ጋር ጥናት ጀመረችና ፈጣን ለውጥ አደረገች። ከቀድሞ ሃይማኖቷ ጋር የነበራትን ማንኛውንም ግንኙነት አቋርጣ ለአምላክ ራሷን መወሰኗን በውኃ ጥምቀት አሳየች። አሁን ከይሖዋ ምሥክሮች አንዷ ሆናለች።”
ሌላዋ እህት ደግሞ እንዲህ ስትል ሪፖርት አድርጋለች፦ “በአጎቴ ሚስት ቀብር ላይ ለመገኘት ሄጄ ነበር። እዚያ እንደደረስኩም አጎቴንና የአጎቴን ልጅ በረሃብ ጠውልገው አገኘኋቸው። የአጎቴ ሚስት ከሞተችበት ዕለት ጀምሮ እህል የሚባል ነገር ባፋቸው አልዞረም ነበር። ለምን እንዳልበሉ ስጠይቃቸው በባሕሉ መሠረት ምግብ ለማብሰል እሳት መጫር እንደማይፈቀድላቸው ነገሩኝ። ከዚያ እኔ ላበስልላቸው ስነሣ አንዳንድ የቤተሰቡ አባላት ይህን አረማዊ ልማድ ብጥስ ሁሉም ሰው ጨርቁን ጥሎ ያብዳል ብለው ፈሩ!”
“ከይሖዋ ምሥክሮች አንዷ እንደመሆኔ መጠን መጽሐፍ ቅዱስ በዘሌዋውያን 18:30 ላይ የሚናገረውን እንደማከብርና ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ወጎችን እንደማልከተል ነገርኳቸው። ከዚያም የሙታን መናፍስት የሚለውን ብሮሹር አሳየኋቸው። ከዚያ ውጥረታቸው ረገብ ሲል ለአጎቴና ለቀሩት ሰዎች ምግቡን አበሰልኩላቸው። የሟቿ ዘመዶች ባሳየሁት ድፍረት ስለተነኩ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማሙ። አሁን ያልተመቁ አስፋፊዎች ሆነው እያገለገሉ ሲሆን መላው ቤተሰብ በቅርቡ እንደሚጠመቁ ተስፋ ያደርጋሉ።”
ሃይማኖታዊ ውሸቶች ያስከተሉትን ግራ መጋባት በተለይም ደግሞ ቅን ሰዎችን አስረው ባሪያ የሚያደርጉትን አስተሳሰቦች የእውነት ንጹሕ ልሳን ድል ሲያደርግ ስናይ እንዴት ደስ ይለናል! የይሖዋ በረከት ታክሎበት ይህ ንጹሕ ልሳን በዛምቢያ አልፎ ተርፎም በመላዋ ምድር እየተስፋፋ ነው።—2 ቆሮንቶስ 10:4
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአገሪቱ የሪፖርት መግለጫ
የ1994 የአገልግሎት ዓመት
የምሥክሮቹ ከፍተኛ ቁጥር፦82,926
ከሕዝቡ ብዛት ጋር ሲነጻጸር፦1 ምሥክር ለ107 ሰዎች
የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች፦363,372
የአቅኚዎች ብዛት በአማካይ፦10,713
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በአማካይ፦108,948
የተጠማቂዎች ብዛት፦3,552
የጉባኤዎች ብዛት፦2,027
ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኝበት ቦታ፦ሉሳካ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሉሳካ ዳርቻ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የቅርንጫፍ ቢሮ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሉሳካ በስተደቡብ በምትገኘው ሺማባላ መስበክ