የአንባብያን ጥያቄዎች
ክርስቲያናዊ ጥምቀት በሚካሄድበት ጊዜ ምን ዓይነት ጠባይ መታየት ይኖርበታል?
ምንም እንኳን አብዛኞቹ አንባቢዎቻችን የተጠመቁ ቢሆኑም እንደሌሎቹ ተጠማቂያን ሁሉ እነርሱንም የሚመለከት ስለሆነ ይህ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። በመጀመሪያ ውኃ ውስጥ በመጥለቅ የሚጠመቁ ግለሰቦችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ እንስጥ። እነዚህ ሰዎች ምን ጠባይ ማሳየት ይገባቸዋል?
ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ተከታዮቹ ወደ አሕዛብ እንዲሄዱና ሰዎችን እያስተማሩና እያጠመቁ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ነግሯቸዋል። ጥምቀት ጊዜያዊ በሆነ የስሜት መነሳሳት ተገፋፍቶ የሚፈጸም ወይም ስሜታዊነት የሚታይበት ድርጊት እንደሆነ አድርጎ አላመለከተም። ከኢየሱስ ምሳሌ እንደምንመለከተው ጥምቀት ከበድ ተደርጎ ሊታይ የሚገባው እርምጃ ነው። ሉቃስ 3:21 “ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። ሲጸልይም ሰማይ ተከፈተ” ይላል። አዎን፣ ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ ጥምቀትን በቁም ነገርና በጸሎት ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል። ከተጠመቀ በኋላ በቅርብ ጊዜ አንዳንዶች እንዳደረጉት ዓይነት ክንዱን ወደ ላይና ወደ ታች እያወዛወዘ ድል ማድረጉን የሚያሳይ ምልክት አሳይቷል ወይም የድል አድራጊነት እልልታ አሰምቷል ብለን ለማሰብ አንችልም። ኢየሱስ እንዲህ አላደረገም፤ መጥምቁ ዮሐንስ ብቻ ባለበት ወደ አባቱ መጸለይ ጀመረ።
መጽሐፍ ቅዱስ ጥምቀት በሕዝበ ክርስትና አንደሚደረገው ዓይነት አንገት የሚቀረቀርበት ወይም ልዩ የሆነ ድግምት የሚደገምበት ወይም መኮሳተርና ፊት ማጥቆር የሚያስፈልግበት ክንውን እንደሆነ አያመለክትም። በሺህ የሚቆጠሩ አይሁድና ወደ ክርስትና የተለወጡ አሕዛብ በክርስቲያናዊ ጥምቀት የተካፈሉበትን የጰንጠቆስጤ በዓል ዕለት አስታውስ። ቀደም ብለው የአምላክን ሕግ ያጠኑና ከእርሱም ጋር ዝምድና የመሠረቱ ነበሩ። ስለዚህ መሲህ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ መማርና መቀበል ብቻ ያስፈልጋቸው ነበር። አንዴ እንዲህ ካደረጉ መጠመቅ ይችሉ ነበር።
ሥራ 2:41 “ቃሉን [“ከልባቸው” አዓት] የተቀበሉ ተጠመቁ” በማለት ይዘግባል። በዌይማውዝ የተዘጋጀው የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ስለዚህ ቃሉን በደስታ የተቀበሉት ተጠመቁ” ይላል። ስለ መሲሑ የሚገልጸውን አስደሳች ዜና በመስማታቸው ተደስተው ነበር። ይህም ደስታቸው በብዙ መቶ በሚቆጠሩ ደስተኛ ተመልካቾች ፊት እንደተፈጸመ በማያጠራጥረው ጥምቀታቸው ላይ ተስተጋብቷል። የሰማይ መላእክት እንኳን ይህን ጥምቀት ተመልክተው ተደስተዋል። ኢየሱስ “ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል” ሲል የተናገረውን ቃል አስቡ።—ሉቃስ 15:10
እያንዳንዳችን የጥምቀትን ክብደትና አስደሳችነት ልናሳይ የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የሚጠመቁ ሰዎች ነጭ ወይም ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ። ይህ ዓይነቱ ልማድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም። በሌላም በኩል በጣም የሚያጣብቁ ወይም ስስ በመሆናቸው እርቃነ ሥጋ የሚያሳዩ የባኞ ቤት ልብሶች ተስማሚ ሊሆኑ አይችሉም። በተጨማሪም ቀደም ብሎ እንደተገለጸው አዲሱ ክርስቲያን ከውኃ እንደ ወጣ ትልቅ ድል እንዳገኘ የሚያሳይ አካላዊ እንቅስቃሴ ማሳየት የለበትም። አዲሱ ሰው በመጠመቁ ምክንያት የቀሩት ክርስቲያን ወንድሞቹ ደስተኞች ናቸው። ይህ የእምነቱ መግለጫ የሆነው ጥምቀት የአምላክን ሞገስ ለማግኘት አቋሙን ሳያጎድፍ መጓዝ ለሚኖርበት ረዥም የሆነ መንገድ የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርበታል።—ማቴዎስ 16:24
በሕዝብ ፊት በሚከናወን የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ላይ የምንገኝ እኛ ተመልካቾችም የሚጠመቀው ሰው ዘመዳችን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪያችን ከሆነ ከደስታው እንካፈላለን። ይሁን እንጂ ከደስታው ሙሉ በሙሉ ለመካፈል ከፈለግን ከጥምቀት እጩዎቹ ጋር ሙሉውን የጥምቀት ንግግር ማዳመጥ፣ የሚቀርቡላቸውንም ጥያቄዎች በግልጽ ሲመልሱ መስማትና ስለ እነርሱ የሚቀርበውን ጸሎት አብረናቸው መከታተል ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን ለጥምቀቱ ትክክለኛ የሆነ የአምላክ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። ጥምቀቱ ከተከናወነ በኋላ መደሰታችንን ለማሳየት የድል አድራጊነት መንፈስ የሚያንጸባርቅ ፈንጠዝያ ማድረግ፣ የአበባ እቅፍ መስጠት ወይም ለተጠማቂው ክብር ግብዣ ማዘጋጀት አያስፈልግም። ነገር ግን ወደ አዲሱ ወንድማችን ወይም እህታችን ቀርበን በወሰዱት አስደናቂ እርምጃ መደሰታችንን ልንገልጽና ሞቅ ባለ ስሜት ወደ ክርስቲያናዊው ወንድማማችነታችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለን ልንቀበላቸው እንችላለን።
እንግዲያው ለማጠቃለል ያህል ሁላችንም ተጠማቂዎችም ጭምር፣ ለጥምቀት የሚገባውን አክብሮትና ክብደት መስጠት ይኖርብናል። ፈንጠዝያ የሚታይበት ወይም እልልታ የሚሰማበት ወይም ድግስ የሚደረግበት ጊዜ አይደለም። በአንጻሩም መኮሳተርና ፊት ማጥቆር አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜም አይደለም። አዳዲስ ሰዎች በዘላለም ሕይወት መንገድ ላይ ከእኛ ጋር ስለ ተሰለፉ መደሰት ይገባናል። አዲሶቹን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በደስታ ልንቀበል እንችላለን።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]