አንድ ምሁር በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ተደነቁ
የጥንታዊው ግሪክ ቋንቋ ምሁር የሆኑት ዶክተር ሬከል ቴን ካት እንደተናገሩት የደች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አንዳንድ ቃላትን በትክክል መተርጎም አልቻሉም። ለምሳሌ በሉቃስ ምዕራፍ 2 ላይ የኢየሱስን እድገት ደረጃ በደረጃ ለመግለጽ የሚያገለግሉ ሦስት የተለያዩ የግሪክኛ ቃላት (ብሬፎስ፣ ፔድዮንና ፔስ) እናገኛለን። እነዚህ ቃላት እያንዳንዳቸው የተለያየ ገጽታ ያለው ትርጉም አላቸው። ነገር ግን በብዙ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ ከእነዚህ ቃላት መካከል ሁለቱ ወይም ሙሉ በሙሉ ሦስቱም በደፈናው “ልጅ” ተብለው ተተርጉመዋል። ትክክለኛው ትርጉም ምንድን ነው?
በቁጥር 12 ላይ ያለው ብሬፎስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ገና የተወለደ ወይም ሕፃን” ማለት ነው። በቁጥር 27 ላይ የገባው ፔዲዮን “ትንሽ ልጅ” ማለት ሲሆን በቁጥር 43 ላይ የሚገኘው ፔስ ደግሞ “ልጅ” ተብሎ መተርጎም አለበት በማለት ዶክተር ቴን ካት አብራርተዋል። ዶክተር ቴን ካት በመጋቢት 1993 የቤበል ኤን ቬተንሻፕ (መጽሐፍ ቅዱስና ሳይንስ) እትም ላይ “እስከማውቀው ድረስ አንድም የደች ትርጉም ይህንን በአጥጋቢ ሁኔታ አልተረጎመም፤ በሌላ አባባል እነዚህ ትርጉሞች ከበኩረ ጽሑፉ ጋር ጨርሶ አይስማሙም” ሲሉ ጽፈዋል።
ከጊዜ በኋላ ዶክተር ቴን ካት ደችን ጨምሮ በ12 ቋንቋዎች የሚገኘውን የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የመመልከት አጋጣሚ አገኙ። የሰጡት አስተያየት ምን ነበር? “ብሬፎስ፣ ፔዲዮንና ፔስ ለሚሉት ሦስት የግሪክኛ ቃላት የተለያየ አጠቃቀም ተገቢውን ትኩረት የሰጠ አንድ የደች መጽሐፍ ቅዱስ በመኖሩ በጣም ተደንቄአለሁ” አሉ። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም እነዚህን ጥቅሶች ከመጀመሪያው የግሪክ ጽሑፍ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ተርጉሟቸዋልን? ዶክተር ቴን ካት “ሙሉ በሙሉ ይስማማል” በማለት ተናግረዋል።