የአምላክ ስም የተቀረጸባቸው ሳንቲሞች
እስቲ እዚህ ላይ የሚታዩትን የብር ሳንቲሞች ቀረብ ብለህ ተመልከታቸው። ሳንቲሞቹ የተሠሩት በጀርመኑ ንጉሠ ነገሥት በዊልኸልም አምስተኛ ከ1627 እስከ 1637 በነበረው የግዛት ዘመኑ ነበር። ወቅቱ መካከለኛው አውሮፓ ሠላሳ ዓመታትን ባስቆጠረው በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል በተደረገው ጦርነት ሙሉ በሙሉ ተዘፍቆ የነበረበት ጊዜ ነበር። ዊልኸልም አምስተኛ ከፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ ጎን ወግኖ ነበር። ይህ ግጭት የሚያስከትለውንም ከፍተኛ ወጪ ለመሸፈን ያለውን ብር ሁሉ ሰብስቦ በማቅለጥ ሳንቲሞች ሠራ።
በጣም የሚያስደንቀው በብዙዎቹ ሳንቲሞች ላይ የተቀረጸው ቅርጽ ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም የሚወክሉት የዕብራይስጥ ፊደላት ዙሪያቸው በፀሐይ ተከቦ የሚያሳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ጥንካሬን የሚወክለው የዘንባባ ዛፍም ተቀርጾ ይገኛል። ይህ የሚያመለክተው ደግሞ ምንም እንኳ ዛፉ በነፋስ ቢያዘምም በአምላክ ጥበቃ ሳይሰበር እንደቀረ የሚጠቁም ነው። በሳንቲሙ ዙሪያ የተቀረጸው የላቲን ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል፦ “ይሖዋ እስከ ፈቀደ ድረስ ትክክለኛ የሆነውን ነገር ማድረጌን እቀጥላለሁ።”
የአምላክን ጥበቃ ለማግኘት ከመለመን ይልቅ ስሙን በዚህ መንገድ መጠቀም ከንቱ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋ በሰው ልጆች ኃይለኛ ግጭቶች መሐል ጣልቃ ገብቶ ወገናዊ አይሆንም። በእርግጥም ሠላሳ ዓመታትን ያስቆጠረው ጦርነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። “አስተማማኝ የሆኑ ግምታዊ አሃዞች አንዳመለከቱት ከሆነ” ይላል ፈንክ ኤንድ ዋግናልስ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ “ገሚሱ የጀርመን ሕዝብ በጦርነቱ አልቋል። ለቁጥር የሚታክቱ የጀርመን ትልልቅና ትንንሽ ከተሞች፣ መንደሮችና የእርሻ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። በግምት ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የጀርመን የኢንዱስትሪ፣ የእርሻና የንግድ ተቋሞች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።”
የይሖዋን ስም በነዚህ ሳንቲሞች ላይ ቀርጸው መጠቀማቸው ለእስራኤል ሕዝብ ተሰጥቶ የነበረን አንድ ትእዛዝ ያስታውሰናል፦ “የአምላክህን የይሖዋን ስም በከንቱ አትጥራ።” (ዘጸአት 20:7 አዓት) ያም ሆነ ይህ እነዚህ ሳንቲሞች ይሖዋ የተባለው መለኮታዊ ስም በጀርመን ይኖሩ በነበሩ ሰዎች ዘንድ ከጥንት ጀምሮ በስፋት የታወቀ እንደነበረ መሥክረዋል። ታዲያ አንተ በዚህ ስም የሚጠራውን አምላክ ምን ያህል ታውቀዋለህ?