ደም የመውሰድ ጉዳይ እንደገና እየተጤነ ነው
በዚህ የኤድስ ጽልመት ባጠላበት ዘመን ለታካሚ ጤንነት ትልቅ ስጋት የሚፈጥር ነገር በሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ክፍል ውስጥ ሊኖር ይችላል። በኬምደን፣ ኒው ጀርሲ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ በሚገኘው በኩፐር ሆስፒታል ዩኒቨርሲቲ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና የሚያደርገውን ማዕከል ከአሥርተ ዓመታት በላይ ሲመሩ የቆዩት ዶክተር ሪቻርድ ስፔንስ “የደም አቅርቦትን ከብክለት ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ የምንችልበት መንገድ የለም” ብለዋል።
ይህ ማዕከል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው ደም አንወስድም በሚል አቋማቸው በስፋት ለሚታወቁት ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የሕክምና አገልግሎት መስጠቱ አያስደንቅም። (ዘሌዋውያን 17:11፤ ሥራ 15:28, 29) ሆኖም ሄፓታይተስ፣ ኤድስ እና ሌሎች በሽታዎችን ጨምሮ ደም መውሰድ ሊያስከትላቸው የሚችላቸው አደጋዎች ያሳሰባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ በርካታ በሽተኞችም ወደ ማዕከሉ ለሕክምና እየመጡ ነው። “የኤድስ ብቅ ማለት ደምን ማጣራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል። ይሁን እንጂ ቫይረሱ በምርመራ ከመገኘቱ በፊት በሰውነት ውስጥ ተደብቆ ሊሆን ስለሚችል በአንዳንድ ሁኔታዎች ደም የማጣሪያ ሂደቱን ሊያልፍ ይችላል” ሲል ኮርየር ፖስት ዊክሊ ሪፖርት ኦን ሳይንስ ኤንድ ሜዲስን የተባለው መጽሔት ዘግቧል።
እንደነዚህ ያሉት አደጋዎች በመኖራቸው ምክንያት ይህ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና የሚያደርግ ማዕከል አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በአንዳንድ ሁኔታዎች የማይቃወሙትን የበሽተኛው ደም ከራሱ ከሰውዬው ተወስዶ ወደ ሰውነቱ ተመልሶ እንዲገባ የማድረግ ዘዴን ጨምሮ ሌሎች አማራጭ ሕክምናዎችን ይጠቀማል።a ሌላው ሕክምና ደግሞ የደም መጠንን ከሚጨምሩ መድኃኒቶች ጋር የተያያዘ ነው። ከዚህም በላይ ደም መውሰድ ሳያስፈልግ አልፎ አልፎ ደምን የሚተኩ መድኃኒቶችን ተጠቅሞ የኦክስጂን አቅርቦትን ማጠናከር ይቻላል። ዶክተር ስፔንስ “የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ሕክምና ይፈልጋሉ፤ ይሁን እንጂ የሚፈልጉት ደም መውሰድን የሚተኩ አማራጭ ሕክምናዎችን ነው” ብለዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ የጸና እምነታቸውን የሚያከብሩ ዶክተሮች ያደረጉላቸውን ትብብርና ድጋፍ ያደንቃሉ። በዚህም ምክንያት በእርግጥም “ጥሩ ሕክምና” አግኝተዋል፤ በተጨማሪም በይሖዋ አምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና መያዝ ችለዋል።—2 ጢሞቴዎስ 1:3
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ይህንን ሂደትና በግል የሚደረግ ሕሊናን የሚመለከት ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቁትን ሁኔታዎች በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ መጋቢት 1, 1989 ገጽ 30–1 ተመልከት።