‘ምናለ ሁሉም ሰው እንደነሱ ቢሆን ኖሮ!’
እነዚህ ቃላት ሉክሰምበርግ ውስጥ የሚታተመው ሌትሰቡርገር ዡርናል የተባለው ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ የተናገራቸው ናቸው። ስለ እነማን እየተናገረ ነበር?
ይህ ጋዜጠኛ በኦሽቪትስ 50ኛ የነፃነት በዓል ላይ ለመገኘት ወደ ፖላንድ ሄዶ ነበር። እዚያም እስካሁን ፈጽሞ ያልተጠቀሰ አንድ ቡድን ከፍተኛ ሥቃይ ደርሶበት እንደነበረ አስተዋለ። የካቲት 2, 1995 ባወጣው አምዱ ላይ ይህ ቡድን የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ገለጸና እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “በጣም ከባድ ቅጣት የሚፈጸምበት እስር ቤትም ሆነ ማጎሪያ ካምፕ፣ በአሠቃቂ ሁኔታ በረሃብ መሠቃየቱም ሆነ በመጥረቢያ ወይም በአንገት መቁረጫ መሣሪያ መገደሉ እምነታቸውን እንዲተዉ አላደረጋቸውም።” በተጨማሪም እንዲህ አለ፦ “ሌላው ቀርቶ ጨካኝ የሆኑት የኤስ ኤስ ወታደሮች እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ሊገደሉ ሲሉ ባሳዩት ድፍረት ተደንቀው ነበር።”
የይሖዋ ምሥክሮች ሰማዕት መሆን አይፈልጉም። ቢሆንም በሺህ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ልክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩ ክርስቲያኖች ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ከማፍረስ ይልቅ ሞትን መርጠዋል። ይህ እምነት ናዚ በገዛባቸው አስከፊ ጊዜያት በጉልህ ተለይተው እንዲታወቁ አድርጓቸዋል።
የአምድ አዘጋጁ “ምናለ ሁሉም ሰው እንደ ይሖዋ ምሥክሮች ቢሆን ኖሮ!” በማለት ደመደመ። ሰዎች ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች ቢሆኑ ኖሮ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በምንም ዓይነት አይከሰትም ነበር።