‘ብረት ብረትን እንደሚስለው’
“ኮፕቲክ ክርስቲያን” እንደሆነ የሚነገርለት አንቶኒ የተባለ ቀናተኛ ወጣት በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ማብቂያ ላይ ዓለም በቃኝ ብሎ ለ20 ዓመታት ከሰው ተገልሎ በምድረ በዳ አሳለፈ። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? አምላክን ለማገልገል የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለ መንገድ ስለመሰለው ነው። አንቶኒ ተሰሚነት የነበረው የሕዝበ ክርስትና የመጀመሪያው ባሕታዊ ወይም መናኝ ነበር።
ሕዝበ ክርስትና ዛሬ ያሏት መናኞች ጥቂት ናቸው። ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች በሌላ መንገድ ራሳቸውን ያገልላሉ። ስለ ሃይማኖት መነጋገር አለመግባባትና ጭቅጭቅ የሚያስከትል ስለሚመስላቸው ከሌሎች ጋር እንዲህ ያለ ውይይት ማድረግ አይፈልጉም። የአምልኳቸው ዋንኛ ክፍል በሰዎች ላይ መጥፎ አለማድረግ ነው።
በሰው ላይ መጥፎ አለማድረግ የእውነተኛው ሃይማኖት አንዱ ክፍል ቢሆንም ይህ ብቻ አይበቃም። አንድ የጥንት ምሳሌ “ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል” ይላል። (ምሳሌ 27:17) መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን የሚያበረታታው ራሳቸውን ከዓለም ወይም ከሌሎች ክርስቲያኖች ሙሉ በሙሉ እንዲያገሉ ሳይሆን እንዲሰባሰቡ ነው። (ዮሐንስ 17:14, 15) “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ . . . መሰብሰባችንን አንተው” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 10:24, 25) የይሖዋ ምሥክሮች ይህንን ምክር ይከተላሉ። የመሰል አማኞችን እምነት በመገንባት ‘አንዱ ሌላውን እንዲስለው’ በሳምንት ውስጥ ብዙ ጊዜያት ይሰበሰባሉ። ቅንነት የተሞላበት የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ማድረግ ወደ ጭቅጭቅ እንደማያመራ አውቀዋል። ከዚህ ይልቅ ወደ ስምምነትና ሰላም ያደርሳል። የእውነተኛው አምልኮ ዐቢይ ክፍል ነው።