“በማይመች አካሄድ አትጠመዱ”
እዚህ ላይ የሚታዩት ሁለት በሬዎች ከባድ ሸክሞችን በቀላሉ ለመጎተት የሚያስችል ከፍተኛ ጥንካሬ አላቸው። ነገር ግን ከበሬዎቹ አንዱ በአህያ ተተካ እንበል። አህያ በመጠንም ሆነ በጥንካሬ ከበሬ ያነሰ ስለሆነ በማይመች ሁኔታ ተጠምደው የሚጎትቱትን ቀንበር በሬው ከላዩ ለመጣል ሙከራ በማድረግ ማስቸገሩ አይቀርም። ስለሆነም ለእስራኤላውያን የተሰጠው የአምላክ ሕግ “በበሬና በአህያ በአንድነት አትረስ” በማለት የተናገረበት ጥሩ ምክንያት ነበረው።—ዘዳግም 22:10
ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎችን በተመለከተ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አንድ ነገር ጽፏል። “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 6:14) በተለይ የትዳር ጓደኛ ስንመርጥ ይህንን በአእምሯችን መያዝ አለብን። ኢየሱስ ክርስቶስ “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” በማለት ስለተናገረ ጋብቻ ቋሚ ጥምረት ነው። (ማቴዎስ 19:6) የትዳር ጓደኛሞች አንድ ዓይነት እምነት፣ መሠረታዊ መመሪያና ግብ ከሌላቸው ከባድ ሐዘን ይደርስባቸዋል። ስለዚህ ‘በጌታ ብቻ’ ስለማግባት የተሰጠውን ምክር መከተሉ ተገቢ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:39) የተለየ ሃይማኖታዊ እምነት ካለው ሰው ጋር የጋብቻ ቁርኝት ማድረግ በሬን ከአህያ ጋር መጥመድ ከሚያስከትለው የከፋ ችግር ያስከትላል።
የሃይማኖታዊ እምነት ልዩነት አንዲት ሴትና አንድ ወንድ በማይመች አካሄድ እንዲጠመዱ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንደኛው ምክንያት ብቻ ነው። ለመጋባት ያሰቡ ጓደኛሞች አንድ ዓይነት እምነት የሚከተሉ ቢሆንም እንኳ ራሳቸውን እንዲህ እያሉ ቢጠይቁ ጥሩ ነው፦ ‘አንድ ዓይነት ግቦች አሉን? የት እንኖራለን? የቤተሰቡን ባጀት የሚሸፍነው ማን ነው? ሁለታችንም እንሠራለንን? ልጆች እንወልዳለንን? ዝምድናችንን የሚቆጣጠሩት ደግነትና አሳቢነት ናቸውን?’
እነዚህ ጥያቄዎች ቁርኝቱ የሚመች ወይም የማይመች መሆኑን በተወሰነ ደረጃ ሊጠቁሙ ይችላሉ። እርግጥ ነው ሁለት ሰዎች በሁሉም ነገር አቻ ይሆናሉ ማለት አይቻልም። ቢሆንም አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሚጠናኑባቸው ጊዜያት ያጋጠሟቸውን ችግሮች መፍታት ከቻሉና ያለምንም ችግር የሐሳብ ግንኙነት ማድረግ ከቻሉ የወደፊቱ ጥምረታቸው ተመጣጣኝ ሊሆን ይችላል።