የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“ከአንድ ወንጌላዊ የሚጠበቀውን ሥራ አከናውን”
ወንጌላዊ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ቃሉ ኢዋጌሊስቴስ የሚለው የግሪክኛ ቃል ትርጉም ነው። ይህ ቃል ደግሞ “የምሥራች” የሚል ትርጉም ካለው ኢዋጌሊዎን ከሚለው ቃል ጋር በጣም ይቀራረባል። ስለዚህ አንድ ወንጌላዊ የምሥራች ሰባኪ ወይም መልእክተኛ ነው።
እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ስለሚያውጁ ወንጌላውያን ናቸው። ጳውሎስ “ከአንድ ወንጌላዊ የሚጠበቀውን ሥራ አከናውን” በማለት ጢሞቴዎስን መምከሩ ተገቢ ነበር። ጢሞቴዎስ ይህንን ሥራ በቁም ነገር መመልከት ነበረበት። ‘በሁሉም ነገሮች የማስተዋል ስሜቶቹን እንዲጠብቅ’ እና ‘አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ እንዲፈጽም’ ጳውሎስ በጥብቅ አሳስቦታል።—2 ጢሞቴዎስ 4:5 አዓት
እኛም ወንጌላውያን እንደመሆናችን መጠን አገልግሎታችንን በቁም ነገር እንመለከታለን እንዲሁም ‘የማስተዋል ስሜቶቻችንን እንጠብቃለን’ ወይም በማንኛውም አጋጣሚ ምሥራቹን ለሰዎች ለማካፈል ዘወትር ንቁዎች እንሆናለን። ብዙዎች ይሖዋንና እርሱ የሰጣቸውን ተስፋዎች ለማወቅ የበቁት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከተገናኙ በኋላ ነው። ባርባዶስ በተባለች አገር የሚኖር ሴሞር የተባለ ሰው ያጋጠመው ይኸው ነው።
ሴሞር በአንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት አስተማሪ ነው። ቻርልስ ደግሞ እዚሁ ትምህርት ቤት ውስጥ ግማሽ ቀን የሚያስተምር ንቁ ወንጌላዊ የሆነ የይሖዋ ምሥክር ነው። ቻርልስ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ወይም አቅኚ ከመሆኑም በላይ እያንዳንዱን አጋጣሚ ምሥራቹን ለሌሎች ለማካፈል ይጠቀምበት ነበር። ሴሞር የመንግሥቱን መልእክት ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማው በቻርልስ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ሴሞርም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን እውነቶች የቻለውን ያህል ለሌሎች ለመናገር ወሰነ። ስለዚህ በሥራ ቦታው ከሚገኙ ሰዎች በተለይ ከተማሪዎቹ ጋር መደበኛ ያልሆነ ውይይት ማድረግ ጀመረ። በአንዳንድ አገሮች በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሃይማኖት ትምህርት ማስተማር ክልክል ቢሆንም ይህ ሰው የሃይማኖትና የግብረገብ ትምህርት እንዲያስተምር ተመድቦ ነበር። አሁን ግን ሴሞር በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረውን የቀድሞ አመለካከት አዲስ ባገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ተክቶ ነበር። በእረፍት ክፍለ ጊዜያት ለተማሪዎቹ ስለ አዲስ ዓለምና ስለ ዘላለም ሕይወት ተስፋ ይነግራቸው ነበር።
ልጆቹ ምን አሉ? ብዙዎቹ ለይሖዋ መንግሥት ምሥራች ልባዊ ፍላጎት አሳዩ። በኋላም ሴሞር 13 ተማሪዎቹን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረ። ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት አመቻቹ። በመጨረሻም አብዛኞቹ በአካባቢያቸው ባለው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። በአሁኑ ጊዜ ዘጠኙ ራሳቸውን ወስ ነው በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ሴሞር ደግሞ የዘወትር አቅኚና ባርባዶስ ውስጥ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ በአንዱ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ እየፈጸመ ነው።
ይህ ተሞክሮ የይሖዋ ምሥክሮች መደበኛ ባልሆነ ምሥክርነት ምሥራቹን ለሰዎች በማካፈል ‘ከወንጌላውያን የሚጠበቀውን ሥራ’ በዓለም ዙሪያ እንዴት ‘እያከናወኑ’ እንዳሉ የሚያሳይ አንዱ ምሳሌ ብቻ ነው። በቆላስይስ 4:5, 6 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ዘመኑን እየዋጃችሁ፣ በውጭ ባሉቱ ዘንድ በጥበብ ተመላለሱ። ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደተቀመመ፣ በጸጋ ይሁን።”