ታላቁ ወዳጃቸው ደግፏቸዋል
ለይሖዋ ምሥክሮች በተለይ የድጋፍ ምንጭ የሆነላቸው አንድ ወዳጅነት አለ። ይህም ከታላቁ ጓደኛ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያላቸው ውድ የሆነ ቅርርብ ነው። (ከያዕቆብ 2:23 ጋር አወዳድር።) እርሱ ታላቅ የእምነት ፈተና በሚያጋጥማቸው ጊዜ ይደግፋቸዋል።
ብዙ ታዛቢዎች የይሖዋ ምሥክሮች በአምባገነን አገዛዞች ሥር ንጹሕ አቋማቸውን ሳያጎድፉ በመኖር ያስመዘገቡትን ታሪክ አድንቀዋል። ከእነዚህ ታዛቢዎች መካከል አንዱ በኮሚኒስት ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በርካታ ዓመታት ካሳለፉ በኋላ በ1968 ከቺኮዝሎቫኪያ ወደ ሌላ አገር የተሰደዱት የፍልስፍና እና የተፈጥሮ ሳይንስ ዶክተር የሆኑት ዪርዢ ክሩፒችካ ናቸው። ሬኔሳንስ ሮዙሙ (የእውቀት ማንሰራራት) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በገለልተኛ አቋማቸው ምክንያት የታሰሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይደርስባቸው ስለነበረው መከራና ስላሳዩት ጽናት ተናግረዋል።
በኮሚኒስቱ አገዛዝ ሥር ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ታስረው ነበር። ምንም እንኳ እስረኛ ቢሆኑም ለጦርነት የሚያገለግለውን ዩራኒየም የተባለ ማዕድን በማውጣቱ ሥራ አንካፈልም ብለዋል። (ኢሳይያስ 2:4) ክሩፒችካ በ1952 ከእነዚህ የማዕድን ማውጫዎች መካከል በአንዱ የተመለከቱትን ነገር ጽፈዋል። በጣም ኃይለኛ በሆነው የክረምት ብርድ ውስጥ በበረዶ የተሸፈኑ ሐውልቶች የሚመስሉ የሁለት ሰዎች ምስል ተመልክተው ነበር። አንገታቸውና ከወገባቸው በላይ ያለው ሰውነታቸው በጠባብ የብረት በርሜሎች ተሸፍኖ ነበር።
ክሩፒችካ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “የተበጣጠቁ የእስር ቤት ልብሶች ለብሰው ከማለዳ ጀምሮ እዚያው ይቆሙ ነበር። እግሮቻቸው በረዶ ሆነው ለረጅም ጊዜ መቆም የቻሉት እንዴት ነው? በእምነት ኃይል ነው። በርሜሎቹ ያረጁና የዛጉ ነበሩ። አንድ ጨካኝ ሰው በርሜሉን ወደታች እንዲጠልቅ ለማድረግ በኃይል ሲጫነው የበርሜሉ የሚዋጋ ክፈፍ የአንዱን ሰውዬ ጃኬት አልፎ ሰውነቱን ተለተለው። ከእጅጌው ውስጥ ደም ይወርድ ጀመር።
“ወታደሩ የነበርኩበትን ረጅም ሰልፍ በእነዚህ ሰዎች ፊት አስቆመና አዛዡ አጠር ያለ ንግግር አደረገልን። አልሠራም ማለት ዓመፅ ስለሆነ የሥራቸውን አግኝተዋል። እነዚህ በጦርነት አንካፈልም የሚሉ የሶሻሊዝም ጠላቶች ስለ ጦርነትና ሰውን ስለ መግደል የሚያቀርቡት የማይረባ ሐሳብ አይጠቅማቸውም በማለት ተናገረ።”
አዛዡ አንድ የብረት ዱላ አነሳና ከሁለቱ በርሜሎች አንዱን መታው። በርሜሉ ውስጥ ያለው ሰውዬ ጭንቅላቱ በበርሜሉ እንደተሸፈነ ተዝለፍልፎ ወደቀ። ቀጥሎ የተከሰተው ነገር በክሩቺፕካ አእምሮ ውስጥ ተቀርጾ ቀርቷል።
እንዲህ አሉ፦ “ክብ ቅርጽ ካላቸው በርሜሎች ውስጥ የሲቃ ድምፅ ይሰማ ጀመር። ከማንኛውም ቦታ ሆኖ ሁሉንም ነገር ለሚሰማው፣ ሌላው ቀርቶ ባረጁትና በዛጉት በርሜሎች ውስጥ የተሰማውን የደከመ ድምፅ ማዳመጥ ለሚችለው አምላክ የሚቀርቡ የሹክሹክታ ጸሎት ይሰማ ነበረ። አምላክ በታላላቅ ካቴድራሎች ውስጥ ከሚዘመሩ መዝሙሮች ይልቅ ይህ ድምፅ ጎላ ብሎ ይሰማዋል።”
በቼክ ሪፑብሊክ ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ሥራ መስከረም 1, 1993 ሕጋዊ እውቅና አግኝቷል። በአሁኑ ጊዜ በቼክ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያቸውን በነፃነት እያከናወኑ ነው። አዎን፣ ስለ ታላቁ ወዳጃቸው ስለ ይሖዋ ለሰዎች መናገሩ ያስደስታቸዋል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቼክ ሪፑብሊክ በተደረገው ስብሰባ ላይ የተገኙ ሰዎች