ሊያመልጥዎ የማይገባ በዓል
“በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት” የሚመጣው ሰማያዊ አባታችን ከሆነው አምላክ ነው። (ያዕቆብ 1:17) አምላክ በኃጢአት ለወደቀው የሰው ዘር ከሰጣቸው ስጦታዎቸ ሁሉ የሚበልጠው በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ከኃጢአት እንድንላቀቅ ያደረገው ዝግጅት ነው። ኢየሱስ ቤዛ ሆኖ ለእኛ መሞቱ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ ከፍቷል። በሉቃስ 22:19 ላይ የእርሱን ሞት እንድናስብ ታዘናል።
የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ትእዛዝ በመከተል ይህንን በዓል አብረዋቸው እንዲያከብሩ ሞቅ ያለ ግብዣ ያቀርቡልዎታል። ይህ ዓመታዊ በዓል በመጽሐፍ ቅዱስ የጨረቃ ቀን አቆጣጠር ኒሳን 14 ማለትም ማክሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 1996 (መጋቢት 24 ቀን እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) ይከበራል። ቀኑን እንዳይረሱት ይመዝግቡት። በአካባቢዎ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባው የሚደረግበትን ትክክለኛ ቦታና ሰዓት ሊነግሩዎት ይችላሉ።