የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የአምላክ ቃል ያለው ሰውን የመለወጥ ኃይል
ጳውሎስ “ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም” እንደነበረ ራሱ ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 1:13) ሆኖም ከጊዜ በኋላ ተለወጠ! ሐዋርያው ጳውሎስ ያደረገው ለውጥ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከጊዜ በኋላ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” ለማለት ችሎ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 11:1
በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ልበ ቅን አምላኪዎች ይህንን የመሰሉ ለውጦች እያደረጉ ነው። እንዲህ ለማድረግ ያስቻላቸው ምንድን ነው? በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውቀት ስለቀሰሙና ያገኙትን እውቀት በኑሯቸው ስለተጠቀሙበት ነው። የሚከተለው ተሞክሮ የአምላክ ቃል ያለውን ሰውን የመለወጥ ኃይል ጎላ አድርጎ ያሳያል።
ስሎቬኒያ ውስጥ በዕድሜ የገፉ አንድ ባልና ሚስት ከመንደር ወጣ ብለው ብቻቸውን ይኖሩ ነበር። ዮዜ ተብለው የሚጠሩት ባልየው ዕድሜያቸው ወደ 60 ዓመት የሚጠጋ ሲሆን ኃይለኛ የመጠጥ ሱስ ነበረባቸው። እንዲህም ሆኖ ሊዩድሚላ የተባሉትን በሽተኛ ሚስታቸውን ያስታምማሉ። አንድ ቀን ሁለት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ወደ ዮዜ ቤት መጡ። ዮዜ ምሥክሮቹ ወደ ቤት እንዲገቡ ጋበዟቸው። ምሥክሮቹ ሲገቡ ከሰውዬው ሚስት ጋር ተገናኙ። ሊዩድሚላ የመንግሥቱን መልእክት ሲሰሙ በፊታቸው ላይ የደስታ እንባ ይፈስ ጀመር። ዮዜም ቢሆኑ በሰሙት ነገር የተደሰቱ ሲሆን ብዙ ጥያቄዎች ጠየቁ። ምሥክሮቹ ለባልና ሚስቱ ጥቂት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አበርክተውላቸው ሄዱ።
ምሥክሮቹ ከአንድ ወር በኋላ ተመልሰው ሲሄዱ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለው መጽሐፍ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ ተመለከቱ። ዮዜ መጽሐፉን ከየት እንዳገኙ ምሥክሮቹ ሲጠይቋቸው “ትታችሁልኝ በሄዳችሁት አንደኛው መጽሔት ጀርባ ላይ አንድ ማስታወቂያ ተመለከትኩና ዛግሬብ ወደሚገኘው ቢሮአችሁ ጽፌ መጽሐፉን አዘዝኩ” ሲሉ መለሱላቸው። ፍላጎታቸውን በመመልከት ተቃርቦ በነበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ እንዲገኙ የጋበዟቸው ሲሆን በዓሉ የተከበረው በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ነበር። ግብዣውን አክብረው በመታሰቢያው በዓል ላይ በመገኘታቸው ምሥክሮቹ ተደሰቱ!
ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩና ጥሩ እድገት አሳዩ። ለምሳሌ ዮዜ “የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውምም” የሚለውን ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሲመለከቱ ወዲያውኑ እቤታቸው ውስጥ የነበሩትን ሃይማኖታዊ ቅርጻ ቅርጾችና ሥዕሎች በጠቅላላ ሰብስበው አስወገዱ።—ዘጸአት 20:4, 5
ዮዜ ለመንፈሳዊ እውነት ያደረባቸው ጥማት በመርካት ላይ ነው። የሚያሳዝነው ግን የመጠጥ ሱሳቸው ገና እንዳለ ነበር። 18 ለሚያክሉ ዓመታት በየቀኑ ወደ 10 ሊትር የሚጠጋ ወይን ይጠጡ ነበር። በጠጪነታቸው የተነሳ ራሳቸውን አይጠብቁም ነበር። ሆኖም አምላክ የአልኮል መጠጥ አላግባብ ስለመውሰድ ያለውን አመለካከት ሲያውቁ ለውጥ ለማድረግ ወሰኑ።
በየቀኑ የሚጠጡትን መጠን በመመዝገብ የመጠጥ ችግራቸውን ቀስ በቀስ ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ብዙም ሳይቆዩ የአልኮል ሱስ ተገዢ ከመሆን ነፃ ወጡ። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው እየገፉ ሲሄዱ እውነተኛ ክርስቲያኖች የግል ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው አወቁ። በዚህ የተነሳ ለምሥክሮቹ ገንዘብ ሰጧቸውና “ሄዳችሁ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ወደ መስክ አገልግሎት ስሄድ የምለብሰው ልብስ ግዙልኝ!” አሏቸው። ምሥክሮቹ የውስጥ ሱሪና ካኔተራ፣ ካልሲ፣ ሸሚዝ፣ ሙሉ ልብስ፣ ከረባት እንዲሁም ቦርሳ ገዙላቸው።
ዮዜ እና ሊዩድሚላ አንድ ዓመት ካጠኑ በኋላ ከምሥክሮቹ ጋር ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ማገልገል ጀመሩ። ከሦስት ወራት በኋላ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ በመጠመቅ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን አሳዩ። ምንም እንኳ ዮዜ ዕድሜያቸው ቢገፋና የተሟላ ጤንነት ባይኖራቸውም ምሥራቹን አዘውትረው ከመስበካቸውም በተጨማሪ ግንቦት 1995 እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ በጉባኤያቸው ውስጥ በዲቁና አገልግለዋል። በእኚህ ትሑት ሰውና በባለቤታቸው ሕይወት ላይ የተገኘው መልካም ውጤት የአምላክ ቃል ሰውን የመለወጥ ኃይል እንዳለው ያሳያል!