የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“ትእዛዛትህ ሁሉ በእውነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው”
ሙሴ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ እስራኤላውያን ሁሉንም የይሖዋ ትእዛዛት እንዲያከብሩ አጥብቆ መክሯቸው ነበር። እንዲህ አለ፦ “የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ይጠብቁና ያደርጉ ዘንድ ልጆቻችሁን እንድታዝዙበት ዛሬ የምመሰክርላችሁን ቃል ሁሉ በልባችሁ አኑሩት። ይህ ነገር ሕይወታችሁ ነው እንጂ ለእናንተ ከንቱ አይደለም።”—ዘዳግም 32:46, 47
ከብዙ ዓመታት በኋላ መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን ለእኔ ቅርብ ነህ፤ ትእዛዛትህ ሁሉ በእውነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው” በማለት የይሖዋ ትምህርቶች ሙሉ በሙሉ አስፈላጊ እንደሆኑ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (መዝሙር 119:151 የ1980 ትርጉም) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ ራሱ ‘ከእግዚአብሔር አፍ የሚወጣ ቃል ሁሉ’ ዋጋ እንዳለው ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:4) ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው” በማለት በአምላክ መሪነት ጽፏል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
ይሖዋ አምላክ በቃሉ ውስጥ ያሰፈረውን መልእክት በጠቅላላ አገልጋዮቹ በቁም ነገር እንዲመለከቱት መፈለጉ አያጠራጥርም። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዋጋ የሌለው አንድም ጥቅስ የለም። ከሞሪሽየስ ከተገኘው ከሚከተለው ተሞክሮ ለማየት እንደሚቻለው የይሖዋ ምሥክሮች ለአምላክ ቃል እንዲህ ያለ አመለካከት አላቸው።
አቶ ዲ—— ገለል ብሎ በሚገኝ በአንድ መንደር ውስጥ የሌሊት ዘብ ሆኖ እየሠራ ይኖር ነበር። ለረጅም ዓመታት አምላክን ለማምለክ የሚያስችለውን ትክክለኛ መንገድ አጥብቆ ይፈልግ ነበር። ተረኛ ዘብ በሚሆንበት ምሽት መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጀመረ። ከዚያም ከዳር እስከ ዳር አንብቦ ጨረሰው። የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ አወቀ። ይህ ስም በሂንዲ ቋንቋ በተዘጋጀው በራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይገኛል። በተለይ የራእይ መጽሐፍ ትኩረቱን ሳበው።
መላውን መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተል ሃይማኖት ይኖር ይሆን በማለት ራሱን ጠየቀ። እርሱ የሚያውቃቸው ሃይማኖቶች ግፋ ቢል የተወሰነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ብቻ እንደሚከተሉ አስተዋለ። አንዳንድ ሃይማኖቶች የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ይቀበሉና የክርስቲያን ግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ጎን ያደርጋሉ። ሌሎች ሃይማኖቶች ደግሞ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ገሸሽ አድርገው የክርስቲያን ግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎችን ብቻ ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።
አንድ ቀን አቶ ዲ—— አንድ ባልና ሚስት ዝናብ ሲመታቸው አየና ወደ ቤቱ ገብተው እንዲጠለሉ ጋበዛቸው። እነዚህ ባልና ሚስት የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ሚስትየው ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል!a የተባለውን መጽሐፍ ይዛ ነበር። አቶ ዲ—— ወዲያውኑ መጽሐፉን እንዲሰጡት ጠየቃቸው። ምሥክሮቹ በራእይ መጽሐፍ ትንቢት ላይ የቀረበው ትምህርት በጣም የሚከብደው መስሎ ስለተሰማቸው ሌላ ጽሑፍ ሰጡት። አቶ ዲ—— ግን ራእይ መጽሐፍን ካልሰጣችሁኝ አለ።
የራሱን ቅጂ አገኘና በአጭር ጊዜ ውስጥ አነበበው። ከዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ምሥክሮቹ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ሲያውቅ ተገረመ። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችና የክርስቲያን ግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች አንድ በአንድ በሚጠኑባቸው በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ይህ ሰው በአሁኑ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪና የተጠመቀ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፉ የታተመው ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ነው።