ይሖዋን በትሕትና አገልግሏል
“ወሳኙ ነገር የምታገለግልበት ቦታና ደረጃ ሳይሆን የምታገለግለው ማንን መሆኑ ነው።” ጆን ቡዝ ብዙ ጊዜ በዚህ አገላለጽ መጠቀም ይወድ ነበር። ደግሞም ሠርቶበታል። ሰኞ ጥር 8, 1996 ያበቃው ምድራዊ ሕይወቱ ማንን ለማገልገል እንደመረጠ በማያሻማ መንገድ አረጋግጧል።
ጆን ቡዝ ገና በለጋነት ዕድሜው በ1921 የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ለማወቅ ይጥር ነበር። በደች የተኃድሶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤት ያስተምር የነበረ ቢሆንም ቀሳውስት የራስ ወዳድነት ሕይወት እንደሚመሩ ይሰማው ስለነበር ቄስ ለመሆን የሚያበቃው ሥልጠና እንዲወስድ የቀረበለትን ሐሳብ አልተቀበለም። “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚል የሕዝብ ንግግር እንደሚቀርብ የሚገልጸውን ማስታወቂያ ሲመለከት እዚያ ላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ እንዲላክለት ለመጠየቅ ምንም ጊዜ አላጠፋም። ባነበበው ነገር ስሜቱ ስለተማረከ በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ይታወቁ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲል 24 ኪሎ ሜትር በብስክሌት ይጓዝ ነበር። በ1923 ተጠምቆ የቤተሰቡ የከብት እርባታ በሚገኝበት በኒው ዮርክ ዎልኪል አካባቢ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመረ።
ወንድም ቡዝ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የጀመረው በሚያዝያ 1928 ነበር። በተወለደበት አካባቢ እንዲሁም በስተደቡብ በሚገኘው ገጠራማ ክፍል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በምግብና በማደሪያ ቦታ በመለወጥ የስብከት ሥራውን አከናውኗል። መሣሪያ መምዘዝ የሚቀናቸው የሕገ ወጥ አልኮል ማጣሪያ ባለቤቶች የሚሰነዝሩትን ማስፈራሪያና የመሳሰሉትን ችግሮች በድፍረት መጋፈጥ አስፈልጎት ነበር። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ተኩሶ የጆን ቡዝን የአቅኚነት ጓደኛ አቁስሎታል። ወንድም ቡዝ በ1935 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል በመሾሙ በአገሪቱ በሙሉ የሚገኙትን ጉባኤዎችና ትናንሽ ቡድኖች መጎብኘት ጀመረ። ትላልቅ ስብሰባዎችን አደራጅቷል፤ እንዲሁም ወንድሞችና እህቶች የሚያጋጥማቸውን ተቃውሞ ተቋቁመው እንዲጸኑ ረድቷቸዋል። በቁጣ የገነፈሉ ሰዎች የሚያነሳሱትን ዓመፅ መጋፈጥ፣ የፍርድ ቤት ሙግቶችና እስር የወንድም ቡዝ የተለመዱ ገጠመኞች ነበሩ። በአንድ ወቅት “በእነዚያ አስደናቂ ጊዜያት የተፈጸሙት ነገሮች ሁሉ ቢዘረዘሩ አንድ መጽሐፍ ይወጣቸው ነበር” ሲል ጽፎአል።
በ1941 በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ወንድም ቡዝ በኢታካ ኒው ዮርክ አቅራቢያ በሚገኘው የመንግሥቱ እርሻ እንዲያገለግል መደበው። በዚያም ለ28 ዓመታት በታማኝነት አገልግሏል። ለአገልግሎት የነበረው ፍቅር ያልቀዘቀዘው ቡዝ እስከ 1961 ድረስ በመንግሥት እርሻው አካባቢ ይገኝ ወደ ነበረውና ሚስዮናውያንን ወደሚያሰለጥነው የመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከሚመጡት በሺህ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ጋር በመገናኘቱ ይደሰት ነበር። ወንድም ቡዝ በ1970 በኒው ዮርክ ዎልኪል በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ እርሻ እንዲያገለግል ሲጠራ ከ45 ዓመታት በፊት የአቅኚነት አገልግሎት ወደ ጀመረበት ቦታ ተመልሶ መምጣቱ ነበር።
ወንድም ቡዝ በ1974 በብሩክሊን ኒው ዮርክ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ። በ93 ዓመት ዕድሜው እስከሞተበት ዕለት ድረስ በዚህ የኃላፊነት ቦታ እምነት የሚጣልበት ሆኖ አገልግሏል። የደግነትንና የትሕትናን ክርስቲያናዊ ባሕርያት የተላበሰው ጆን ቡዝ ተወዳጅ ሰው ነበር። ጤንነቱና ጉልበቱ እስከ ከዳው ዕለት ድረስ ከቤት ወደ ቤት በመሄድና በከተማው መንገዶች ላይ በመጓዝ በታማኝነት ሲሰብክ ቆይቷል።
አብረውት ሲያገለግሉ የነበሩ በእርሱ ማለፍ ቢያዝኑም መጽሐፍ ቅዱስ እንደ እርሱ ያሉትን ቅቡዓን አስመልክቶ ሰማያዊ ሕይወት ለማግኘት እንደሚነሡና ‘ሥራቸውም እንደሚከተላቸው’ በሚሰጠው ተስፋ ይጽናናሉ። (ራእይ 14:13፤ 1 ቆሮንቶስ 15:51-54) ጆን ቡዝ የሄደው አዲስ ወደሆነ አካባቢና ሁኔታ ቢሆንም በዚያ ይሖዋን ለዘላለም ለማገልገል ይችላል!
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆን ቡዝ 1903-1996
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
HERALD-AMERICAN, ANDOVER 1234
76 Jehovites Jailed in Joliet
[ምንጭ]
Chicago Herald-American