ሐኪሞች ያለ ደም ሕክምና በሚሰጥበት ጉዳይ ላይ ተማከሩ
ከተለያዩ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች የተውጣጡ 200 የሚሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች በሕክምናው መስክ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ በመጣው ርዕሰ ጉዳይ ማለትም ያለ ደም ሕክምና መስጠትና ቀዶ ሕክምና ማድረግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ለመወያየት ቅዳሜ ጥቅምት 7, 1995 በክሌቭላንድ ኦሃዮ ውስጥ ስብሰባ አድርገው ነበር።
በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውይይት ተደረገባቸው። ለምሳሌ አንድ ሰው ኃይለኛ ደም ማነስ ቢኖርበት ምን ሊደረግ ይቻላል? አንድ ሕፃን ያለጊዜው ቀደም ብሎ ቢወለድ ያለ ደም እንዴት ሕክምና ሊደረግለት ይቻላል? ደም ሳይሰጥ በተሳካ ሁኔታ የልብ ቀዶ ሕክምና ማከናወን ይቻላልን? የሚያስገርመው ግን ሰውነት የራሱን የደም መጠን እንዲጨምር የሚያስችል ዘዴ በመጠቀም እነዚህ ሁሉ ችግሮች የነበሯቸው ሰዎች ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸው አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል።a
ደም በመስጠት ከሚከናወነው ሕክምና ሌላ አማራጭ ያስፈለገው ለምንድን ነው? “ደም መውሰድ የተለያዩ በሽታዎችን በተለይ ሄፓታይተስ የተባለውን በሽታ እንደሚያስተላልፍ ተረድተናል” በማለት በክሌቭላንድ ውስጥ በሴንት ቪንሰንት ቻሪቲ ሆስፒታል ደም አልባ መድኃኒቶችና ቀዶ ሕክምና የሚሰጠው ማዕከል ዲሬክተር የሆኑት ሻሮን ቬርኖን ተናግረዋል። “የተወሰደው ደም በሽታ ባያስተላልፍም እንኳን የበሽተኛውን በሽታ የመቋቋም ተፈጥሯዊ አቅም ሊያዳክመው ይችላል” በማለት አክለው ተናግረዋል። ኤድስ በደም የሚተላለፍበትን ሁኔታ ደምን በመመርመር እንዲቀንስ ቢደረግም በዚህ የምርመራ ዘዴ ሊታዩ የማይችሉ አሁንም ገና ብዙ በሽታዎች አሉ። ምንም እንኳ ያለ ደም የሚከናወነው ቀዶ ሕክምና ተጨማሪ ዝግጅት ማድረግ የሚጠይቅ ቢሆንም የተበከለ ደም ለሕሙማን በሚሰጥበት ጊዜ ሆስፒታሎች በሕግ ተጠያቂ ሆነው የሚያወጡትን ወጪ በማስወገድ ረገድ ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል።
የይሖዋ ምሥክሮች ደም የማይወስዱበት ከዚህ የበለጠ ሌላ ምክንያት አላቸው። የአምላክ ሕግ ደም መውሰድን በጥብቅ ያወግዛል። (ሥራ 15:29) ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉ በተሻለ የሕክምና ዘዴ ለመጠቀም ይፈልጋሉ። በዚህም ምክንያት ያለ ደም ሕክምና መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ምርምር ከሚያደርጉ ዶክተሮች ጋር ይተባበራሉ። እንዲህ ያለው ሕክምና የሚጠቅመው የይሖዋ ምሥክሮችን ብቻ ሳይሆን ደም በመውሰድ ምክንያት ሊከተል የሚችለውን አደጋ በመፍራት ለሚጨነቁ ሌሎች ብዙ ሰዎችም ጭምር ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የኅዳር 22, 1993 ገጽ 24-27 እና የጥር 22, 1996 ገጽ 31 የእንግሊዝኛ ንቁ! እትሞች ተመልከት።
[ምንጭ]
WHO photo by P. Almasy