“አታባሯቸው!”
“የይሖዋ ምሥክሮች እቤታችሁ መጥተው በራችሁን ቢያንኳኩ አታባሯቸው!” በማለት ኮሪዬር ዴላ ሴራ የተባለ ጋዜጣ ምክር ይለግሳል። ጋዜጣው እንዲህ ብሎ የተናገረው ከኢጣሊያ በስተ ሰሜን ትሬቪዞ በሚባል ቦታ የሚኖር አንድ ነጋዴ እቤቱ የመጡትን ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በማባረሩ ምክንያት ከአንድ ሚልዮን የሚበልጥ ሊሬ (ከ600 የአሜሪካ ዶላር በላይ) ሊያጣ እንደነበረ የሚገልጽ ዘገባ ባወጣበት ጊዜ ነበር።
“የዛሬው ዕለት ላንተ ልዩ ቀን ነው። እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ነን። ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር ልንሰጥህ መጥተናል” በማለት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን ለአንድ ሰው እንዳስተዋወቁ ጋዜጣው ዘግቧል። የተበሳጨው ነጋዴ ንግግራቸውን ገና ሳይጨርሱ በሩን በላያቸው ላይ ጠረቀመው።
ሰውየው አዳምጧቸው ቢሆን ኖሮ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች በአንድ መናፈሻ አግዳሚ ወንበር ላይ ያገኙትን የገንዘብ ቦርሳ ሊመልሱለት እንደመጡ ይረዳ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮቹ የገንዘብ ቦርሳውን ከነገንዘቡ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ከመስጠት የተሻለ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። በሚቀጥለው ቀን ፖሊሶች የገንዘቡን ቦርሳ ለባለቤቱ አስረከቡ።
“ሌላ ሰው በእነዚህ ምስኪን [የይሖዋ ምሥክሮች] ቦታ ቢሆን ኖሮ በቦርሳው ውስጥ ያለውን ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ . . . ለራሱ ሊያስቀር ይችል ነበር” በማለት ኢል ጋዜቲኖ ዲ ትሬቪሶ ተናግሯል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉ በሙሉ ሐቀኞች ስለሆኑ እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አያደርጉም።
የይሖዋ ምሥክሮች “ሙሉ በሙሉ ሐቀኞች” እንዲሆኑ የገፋፋቸው ምንድን ነው? ከኢየሱስ ትምህርት ጋር በመስማማት ለአምላክና ለሰዎች የሚያሳዩት ፍቅር ነው። (ማቴዎስ 22:37-39) ይሖዋ አምላክ አመጣዋለሁ ብሎ ቃል ስለ ገባው አስደናቂ “አዲስ ምድር” የሚገልጸውን ምሥራች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የሚያውጁትም በዚህ ምክንያት ነው። እንዲህ ያለው የተስፋ መልእክት ከማንኛውም ቁሳዊ ሀብት በጣም የላቀ ነው!—2 ጴጥሮስ 3:13