ስለ ጥፋት ውኃ የሚናገሩት አፈ ታሪኮች የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ ይደግፋሉ
በኖህ ዘመን የደረሰው ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በታሪክ የተረጋገጠ ሐቅ ነው። በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ሕዝቦች ስለ ጥፋት ውኃ የሚተርኩ አፈ ታሪኮች አሏቸው። በአፍሪካዊቷ አገር በቻድ የሚኖሩ ሙሴይ የሚባለው ጎሳ አባሎች ስለ ጥፋት ውኃ እንዲህ ብለው ይናገራሉ፦
‘ድሮ ድሮ በአንድ ሩቅ አገር አንድ ቤተሰብ ይኖር ነበር። አንድ ቀን የዚህ ቤተሰብ እናት ለቤተሰቡ ድል ያለ ድግስ ማዘጋጀት ፈለገች። ከዚያም ማሽላ ለመውቀጥ ሙቀጫና ዘነዘና ወሰደች። በዚያን ጊዜ ሰማይ እንደ አሁኑ ሩቅ ሳይሆን በጣም ቅርብ ነበር። እንዲያውም እጃችሁን ወደ ላይ ብትዘረጉ ሰማዩን መንካት ትችሉ ነበር። እርሷም ባላት ኃይል ሁሉ ተጠቅማ ስትወቅጠው ማሽላው ወዲያው ዱቄት ሆነ። ይሁን እንጂ በምትወቅጥበት ጊዜ በግዴለሽነት ዘነዘናውን ወደ ላይ በጣም በማንሳቷ ሰማዩን ሸነቆረችው! ወዲያውም ብዙ ውኃ ወደ ምድር መፍሰስ ጀመረ። ይህም እንዲያው ተራ ዝናብ አልነበረም። ጠቅላላው ምድር በውኃ እስኪሸፈን ድረስ ለሰባት ቀንና ለሰባት ሌሊት ዘነበ። ዝናቡ በሚዘንብበት ጊዜ ሰማዩ አሁን እንዳለው ወደ ማይደረስበት ቦታ እስኪደርስ ድረስ ወደ ላይ ከፍ ማለት ጀመረ። በሰው ልጆች ላይ የደረሰ እንዴት ያለ አሳዛኝ ጥፋት ነው! ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በእጃችን ሰማዩን የመንካት ልዩ መብት አጣን።’
የሚያስደንቀው ነገር ስለ ዓለም አቀፉ የጥፋት ውኃ የሚነገሩ ጥንታዊ አፈ ታሪኮች በዓለም ዙሪያ ማግኘት ይቻላል። በአሜሪካ የሚኖሩ ሕዝቦችም ሆኑ በአውስትራሊያ የሚኖሩ አቦርጂኖች ሁሉም ስለ ጥፋት ውኃ የሚናገሩ ታሪኮች አሏቸው። ዝርዝር ማብራሪያው የተለያየ ቢሆንም ብዙዎቹ ምድር በውኃ ተሸፍና እንደነበርና ጥቂት ሰዎች ብቻ ሰው ሰራሽ መርከብ ውስጥ ገብተው በሕይወት እንደተረፉ የሚገልጹ ዘገባዎችን ይዘዋል። እንዲህ ያለ ተመሳሳይ አነጋገር በሰፊው መሰራጨቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበው ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ በትክክል መከሰቱን የሚያረጋግጥ ነው።—ዘፍጥረት 7:11-20