ልብ የሚነካ መጽሔት
የአንባብያንን የእውቀት ጥማት ወይም የመዝናናት ፍላጎት ለማርካት በዓለም ዙሪያ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መጽሔቶች ይታተማሉ።
በእጅህ የያዝከውን መጽሔት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? በጀርመን ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የደረሰን የሚቀጥለው ደብዳቤ ለዚህ መልስ ሊሰጥ ይችላል፦
“ውድ ወንድሞች፣ ለምታደርጉት ጥረትና ለምታከናውኑት ሥራ ከልብ አመሰግናችኋለሁ። እኔና ሁለት ልጆቼ ከስብሰባ ወደ ቤታችን ከተመለስን በኋላ ምንም እንኳ ሰዓቱ ከምሽቱ 3:30 ቢሆንም በቅርቡ የወጣውን መጠበቂያ ግንብ [በካሴት] መስማት ነበረብኝ። ዕቃ እያጠብኩ የመጀመሪያውን የጥናት ርዕስ ማዳመጥ ጀመርኩ። (የሚያዝያ 1, 1995 እትም) እንደገና ማዳመጥ እንዳለብኝ ስለ ተሰማኝ የወጥ ቤት ሥራዬን አቋርጬ ካሴቱን እየሰማሁ [“በአምላክ ፊት ውድ ናችሁ!” የሚለውን] የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕሱን አነበብኩ። በተለይ አራተኛውና አምስተኛው አንቀጾች በጣም ልቤን ነኩኝ። ከዚያም እንባዬ ይፈስስ ጀመር፤ ሆኖም ይህ ሁኔታ ብዙም አልቆየም። በሕይወት በመኖሬ፣ ከሕዝቦቹ አንዷ በመሆኔና ከሌሎች ጋር ሆኜ ስሙን ለማሳወቅ በመቻሌ ይሖዋን አመሰገንኩት። በእርግጥም ምንም ዋጋ እንደሌለን እንዲሰማን የሚያደርግ አንዳችም ምክንያት የለም። ይሖዋ ለሕዝቡ መንፈሱን ሰጥቷል። ሁላችንም በአንድነት እንጽና፣ በእምነት ጠንክረን እንቁም። ከክርስቲያናዊ ፍቅር ጋር ሞቅ ያለ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ፤ የእምነት እህታችሁ።
መጠበቂያ ግንብ ከእውቀት የበለጠ ነገር ይሰጣል። የአንባብያኑን ልብ ከመንካቱም በተጨማሪ መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን የሚያረካና ወቅታዊ ማበረታቻ የሚሰጥ ነው። አዎን፣ መጠበቂያ ግንብ “በተገቢው ጊዜ ምግብ” ያቀርባል።—ማቴዎስ 24:45 አዓት