በአራት የጦርነት ዓመታት የተገኘ ማጽናኛ
በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ክልል ለአራት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ብዙ ሰዎች ከባድ መከራ የደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ በብዙ ነገሮች የአቅርቦት እጥረት ተሠቃይተዋል። ከእነዚህም መካከል “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” የሆነውን ይሖዋን በታማኝነት ማምለካቸውን የቀጠሉት በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል።—2 ቆሮንቶስ 1:3
በሳራዬቮ የሚኖሩ ሰዎች በጦርነት ጊዜ ሁሉ ተከብባ በነበረች ትልቅ ከተማ ውስጥ መኖር የሚያስከትለውን ተጨማሪ ችግር አሳልፈዋል። የኤሌክትሪክ፣ የውኃ፣ የማገዶ እንጨትና የምግብ እጥረት ነበር። በሳራዬቮ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ በእነዚህ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ሥራውን ማካሄድ የቻለው እንዴት ነው? በጎረቤት አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል ከፍተኛ መጠን ያላቸው የእርዳታ ቁሳቁሶች አምጥተውላቸዋል። (የኅዳር 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 23-7 ተመልከት።) በተጨማሪም በሳራዬቮ የሚኖሩ ወንድሞች መንፈሳዊ ነገሮችን ለማካፈል ቅድሚያ በመስጠት ያለቻቸውን ነገር እርስ በርሳቸው ይከፋፈሉ ነበር። ከተማዋ ተከባ በነበረበት ወቅት በዚያ የሚኖር አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች የሚከተለውን ሪፖርት ልኳል፦
“ስብሰባዎቻችንን እጅግ ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። ሚስቴና እኔ እንዲሁም ሌሎች 30 ሰዎች አንድ ላይ ሆነን ወደ ስብሰባው ቦታ ለመድረስ 15 ኪሎ ሜትር [9 ማይል] በእግራችን እንጓዛለን። ውኃ የሚታደልበት ሰዓት ለሕዝቡ በማስታወቂያ ይነገር ነበር፤ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ እኛ ስብሰባ የምናደርግበትና ውኃ የሚታደልበት ሰዓት ይገጣጠም ነበር። በዚህ ጊዜ ወንድሞች ምን ያደርጋሉ? እቤት ይቀራሉ ወይስ ወደ ስብሰባ ይሄዳሉ? ወንድሞች በስብሰባዎቹ ላይ መገኘት መርጠዋል። ወንድሞች ሁልጊዜ እርስ በርስ ይረዳዳሉ፤ ያላቸውን ነገር ሁሉ ለሌላው ያካፍላሉ። በጉባኤያችን ያለች አንዲት እህት የምትኖረው በከተማው ዳር በጫካው አቅራቢያ ነው፤ ስለዚህ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ለማግኘት ከሌላው ትንሽ የተሻለ አጋጣሚ ነበራት። በተጨማሪም የምትሠራው በአንድ ዳቦ ቤት ነው፤ የሚከፈላት ደሞዝ ደግሞ ዱቄት ነው። አጋጣሚውን በምታገኝበት ጊዜ አንድ ትልቅ ዳቦ ትጋግርና ወደ ስብሰባው ይዛ ትመጣለች። ከስብሰባው በኋላ ወደ ቤት ልንሄድ ስንነሳ ለሁሉም ቆርሳ ታከፋፍላለች።
“እንደተተዉ ሆኖ የሚሰማቸው ወንድሞች ወይም እህቶች አለመኖራቸው ጥሩ ነው። ነገ በአስቸጋሪ ሁኔታ ሥር ወድቆ እርዳታ የሚያስፈልገው ማን እንደሆነ የሚያውቅ የለም። መንገዶች በበረዶ በሚሸፈኑበት ጊዜና አንዲት እህት በምትታመምበት ጊዜ ወጣቶችና ጠንካሮች የሆኑ ወንድሞች በበረዶ ላይ በሚንሸራተት ጋሪ እየገፉ ወደ ስብሰባ ያመጧታል።
“ሁላችንም በስብከቱ ሥራ እንካፈላለን፤ ይሖዋም ጥረታችንን ባርኮታል። በቦስኒያ ውስጥ በምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ሥር እንዳለን ተመልክቷል፤ ሆኖም ከጦርነቱ በፊት አይተነው የማናውቀው ጭማሪ እንድናገኝ በማድረግ ባርኮናል።”
በተመሳሳይም በጦርነት በታመሱ ሌሎች የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ክፍሎች የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ መከራ ቢደርስባቸውም እንኳ ጭማሪ አግኝተዋል። በክሮኤሽያ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ አንድን የምሥክሮች ቡድን አስመልክቶ የሚከተለውን ሪፖርት ልኳል፦ “በቬሊካ ክላዱሻ የሚኖሩ ወንድሞች ከባድ የመከራ ጊዜያት አሳልፈዋል። ከተማዋ በተደጋጋሚ ጊዜያት ጥቃት ደርሶባታል። ወንድሞች ለክሮአቶች፣ ለሰርቦችና ለተለያዩ የሙስሊም ጦር ሠራዊቶች ያላቸውን የገለልተኝነት አቋም ማስረዳት አስፈልጓቸዋል። እንደ መታሰር፣ መደብደብ፣ ረሃብና የሞት አደጋ ያሉ ብዙ መከራዎችን መቋቋም ነበረባቸው። አሁንም ቢሆን ሁሉም በታማኝነት አቋማቸው ጸንተዋል፤ በሥራቸውም ላይ የይሖዋ በረከት ሲፈስ የማየት ልዩ መብት አግኝተዋል።”
በቬሊካ ክላዱሻና በአቅራቢያቸው በምትገኘው በቢሃች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህ መከራዎች ቢደርሱባቸውም የአምላክን አጽናኝ መልእክት በቅንዓት ለሰዎች በማካፈል ጭማሪ ማግኘታቸውን ቀጥለዋል። በእነዚህ ሁለት ቦታዎች የሚኖሩ 26 የመንግሥቱ አስፋፊዎች 39 የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመምራት ላይ ናቸው!