‘ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት ይፈልጋሉ’
ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ከላይ ያለውን የተናገረው አንድ የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ ነው። ይህንን የተናገረው ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የሙሉ ጊዜ ነፃ አገልግሎት ከሚሰጡት መካከል አንዷ ለሆነችው ለካተሊን ነበር።
ካተሊን ፀሐይዋ ፍንትው ብላ በወጣችበት በአንድ ሞቃታማ የበልግ ቀን በምሣ የዕረፍት ጊዜዋ በቤቴል አቅራቢያ በሚገኝ አንድ መናፈሻ ውስጥ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጣለች። የጆሮ ማዳመጫ አድርጋ ቴፕ እየሰማች ነበር። ከተማዋን ሲጎበኙ የነበሩት ሊቀ ጳጳስ ሊሄዱ ስለነበር ከኢስት ወንዝ ማዶ በሚገኘው የሄሊኮፕተር ማረፊያ ዝግጅት እየተደረገ ነበር። በየቦታው ጥበቃው ተጠናክሯል፤ በርካታ ፖሊሶች በመናፈሻው አካባቢ ይዘዋወራሉ። ከእነርሱ መካከል አንዱ ወደ ካተሊን ቀረብ ብሎ ምን እያደረገች እንዳለ ጠየቃት። ካተሊንም እንዲህ ስትል መለሰችለት፦ “የሩሲያ ቋንቋ የተቀዳበት ክር እያዳመጥኩ ነው። አየህ እኔ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዷ ነኝ፤ በመሆኑም እዚህ ከተማ ውስጥ ለመኖር ለመጡት የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማካፈል እንድችል የሩሲያ ቋንቋ ለመማር እፈልጋለሁ።”
ፖሊሱም በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በየቦታው ለጥበቃ እየተዘዋወረ በሠራባቸው 15 ዓመታት ለይሖዋ ምሥክሮች ያለው አድናቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደመጣ ነገራት። “የይሖዋ ምሥክሮችን የምመለከታቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ሰዎች ለመርዳት ከልባቸው የሚጥሩ አባላት እንዳሉት የተደራጀ ሃይማኖት አድርጌ ነው።”
የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት በሚያደርጉት የስብከት ሥራ በዓለም ዙሪያ የታወቁ ናቸው። (ሥራ 20:20) የሰው ልጆችን ቀስፈው ለያዙት ችግሮች ሁሉ ብቸኛ መፍትሔ የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ከመጠቆማቸው በተጨማሪ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታቸው ውስጥ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በማበረታታት ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ይረዷቸዋል። ለምሳሌ ያህል ምሥክሮቹ በቤታቸው ውስጥ ለመማር አመቺ የሆነ ሁኔታ እንዲፈጥሩ ወላጆችን ያበረታቷቸዋል። ግለሰቦች አንድ አሠሪ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውን ችሎታዎችና ባሕርያት እንዲያፈሩ በማበረታታት ሐቀኞችና ሕግ አክባሪዎች እንዲሆኑ ይመክራሉ።
አዎን የይሖዋ ምሥክሮች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ለመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ቀጥሎ ለቀረበው ግብዣ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ እናበረታታዎታለን።