የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 12/15 ገጽ 20-21
  • “ታዲያ ቤተ ክርስቲያናችሁ የት ነው?”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ታዲያ ቤተ ክርስቲያናችሁ የት ነው?”
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 12/15 ገጽ 20-21

“ታዲያ ቤተ ክርስቲያናችሁ የት ነው?”

በሞዛምቢክ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ ይህ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል። ስለ ጉዳዩ በግልጽ ለመናገር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህን ጥያቄ መመለስ አስቸጋሪ ነበር። ይህ የሆነው የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ አገር ውስጥ እስከ 1991 ሕጋዊ እውቅና ስላልነበራቸው ነው። ስለዚህ በግልጽ የሚታወቁ የተወሰኑ የአምልኮ ቦታዎች መሥራት አልተቻለም ነበር።

ሆኖም የካቲት 19, 1994 ሁኔታው ተለወጠ። በዚያ ሞቃታማና ፀሐያማ ቀን በሞዛምቢክ የመጀመሪያዎቹ ሁለት የመንግሥት አዳራሾች ለአምላክ አገልግሎት እንዲውሉ የተደረገበት ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል። በሞዛምቢክ ጠረፍ አማካይ ቦታ ላይ ቤራ በተባለው የወደብ ከተማ ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ግሩም የሆኑ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ለአምላክ አገልግሎት ለማዋል በተካሄደው በዚህ ፕሮግራም ላይ 602 ሰዎች ተገኝተዋል። እነዚህ አዳራሾች በዚህች ከተማ ለሚገኙ ሦስት ጉባኤዎች ያገለግላሉ።

መሠረት ከመጣል አንሥቶ ሕንፃዎቹን እስከ ማጠናቀቅ ድረስ ጠቅላላው ፕሮጄክት አንድ ዓመት ከሁለት ወር የሚያህል ጊዜ ፈጅቷል። ብዙውን ጊዜ 30 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ከዚምባቡዌ መጥተው በአካባቢው ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር እጅ ለእጅ ሆነው ይሠሩ ነበር። የሥራው እንቅስቃሴ ማዕከል የነበረው በቤራ የሚገኘው የሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ሁሉንም ሊያስተናግድ ስላልቻለ አንዳንዶቹ ቅዳሜና እሑድ እና አንዳንድ ጊዜ በሳምንቱ መካከል በቤቱ ዙሪያ ድንኳን ተክለው ያድሩ ነበር።

የማሳምባና ሙንሃቫ ጉባኤዎች የመንግሥት አዳራሽ የሚገኘው በቤራ ዋና ጎዳና ላይ ነው። አንድ ሚስዮናዊ እንዲህ ብሏል፦ “ሥራው እየተፋጠነ ሄዶ እድገቱ በግልጽ በሚታይበት አንድ ሥራ የበዛበት ቀን በአካባቢው የሚያልፉ ሹፌሮች የመንግሥት አዳራሹን ሲመለከቱ ከትራፊክ አደጋ ለጥቂት እንደዳኑ አይተናል።” ብዙዎች ቆም ብለው በመካሄድ ላይ ያለውን ሥራ ያያሉ፤ በተለይ የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች በኅብረት መሥራታቸው ትኩረታቸውን ይስበው ነበር።

ሥራው ብዙ እቅድና አደረጃጀት የሚጠይቅ ነበር። በዚህ አገር ውስጥ የሚካሄዱ ሌሎች ፕሮጄክቶች በዕቃና በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሲቆሙ የመንግሥት አዳራሾቹ ሥራ አቅርቦት በማጣት አልተቋረጠም ነበር። በአንድ ወቅት 800 ከረጢት ሲሚንቶ ያስፈልግ የነበረ ቢሆንም ሲሚንቶ ማቅረብ የሚችለው ብቸኛ ፋብሪካ የሚበቃውን ያህል የሲሚንቶ ወረቀቶች አልነበሩትም። ወንድሞች በዋና ከተማው በማፑቶ ለሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ስለ ሁኔታው ከገለጹ በኋላ የሲሚንቶ ወረቀቶቹ በአውሮፕላን ተላኩና ወደ ሲሚንቶ ፋብሪካው ተወስደው ሲሚንቶ ተሞሉ። ሥራው ሳይቋረጥ ቀጠለ።

በሌላ ወቅት ደግሞ ጣሪያው እየተዋቀረ ሳለ ሠራተኞቹ የብረት እጥረት አጋጥሟቸው ነበር። በአካባቢው ከፍተኛ የብረት እጥረት ስለ ነበረ ቀደም ሲልም ቢሆን ለፕሮጄክቱ የሚሆን ብረት የመጣው 600 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኝ ቦታ ነበር! ከሠራተኞቹ አንዱ የግንባታውን ሥራ ቆሞ ሲመለከት ወደ ነበረ ሰው ጠጋ ብሎ ሥራውን ለማጠናቀቅ የሚያስችል ብረት ከየት ሊያገኙ እንደሚችሉ ያውቅ እንደሆነ ጠየቀው። ሰውዬው እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ከአንድ ሰዓት በላይ ለሚያህል ጊዜ እዚህ ቆሜ ነበር፤ ይህን ያደረግሁት ደግሞ እንዲሁ ባጋጣሚ አይመስለኝም። የምትሠሩትን ሥራና የፕሮጄክቱን መንፈስ ሳላደንቅ ላልፍ አልቻልኩም። እናንተ የምትፈልጉት ዓይነት ብረት ስላለኝ በስጦታ መልክ ብለግሳችሁ ደስ ይለኛል።” ይህም በወቅቱ በጣም የሚያስፈልግ ነበር።

ብዙ ሰዎች ሕንፃዎቹን የሚያሠራው ምን ያህል ትልቅ የሕንፃ ሥራ ድርጅት ቢሆን ነው ብለው ተደንቀው ነበር። ሠራተኞቹ በነፃ አገልግሎት የሚሰጡ የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን መግለጽ ያስደስታቸው ነበር። የተመልካቾቹን ትኩረት ይበልጥ የሳበው ምንድን ነው? ከተመልካቾቹ አንዱ “በጣም የምትተባበሩ ሰዎች ናችሁ። ምንም እንኳ ከተለያየ ዘር የተውጣጣችሁ ብትሆኑም በወንድማማችነት መንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።” በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ለመጠየቅ መጥተዋል። በተጨማሪም በስብሰባዎች ላይ ብዙ ለውጥ አምጥቷል። ለምሳሌ ያህል የማንጋ ጉባኤ አማካይ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ከምሥክሮቹ ቁጥር በእጥፍ የሚበልጥ ነው።

አዲሶቹ የመንግሥት አዳራሾች በአካባቢው ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ በረከት እንደሆኑላቸው አያጠራጥርም። ቀደም ሲል አብዛኞቹ ይሰበሰቡ የነበሩት የሣር ክዳን ባላቸው ቤቶች ወይም ጓሮ ትንሽ የቆርቆሮ ጣሪያ አበጅተው ወይም በግል መኖሪያ ቤት አነስተኛ ክፍል ውስጥ ነበር። ብዙውን ጊዜ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት በውኃ ይበሰብሱ ነበር፤ ሆኖም ከስብሰባ ፈጽሞ ቀርተው አያውቁም። ለብዙ አሥርተ ዓመታት በሞዛምቢክ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያውቋቸው “የመንግሥት አዳራሾች” እነዚህ ብቻ ነበሩ። የማሳምባ ጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ወንድም ኪታኑ ገብርኤል “ይህ ፕሮጄክት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያደረጉትን በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞቻችንን እናመሰግናቸዋለን” ብሏል። አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “በካሪኩ (የይሖዋ ምሥክሮች ለ12 ዓመታት ያህል ታስረው የነበሩባቸው “የተሐድሶ ትምህርት መስጫ ካምፖች”) በነበርንባቸው ጊዜያት ‘በታማኝነት ከጸናን ይሖዋ ወሮታችንን ይከፍለናል’ እንል ነበር። አዲሱ የመንግሥት አዳራሽ ከይሖዋ የተገኘ ወሮታ ነው።” እነዚህ ቃላት ምሥክሮቹ በጣም አመስጋኞች እንደሆኑና ይሖዋን ለማወደስ ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረጉ ይጠቁማሉ።

በግንባታው ሥራ የተሳተፉ ብዙ ወጣቶች የአቅኚነት መንፈስ አድሮባቸው ከዚያ በኋላ ወደ ዘወትር አቅኚነት አገልግሎት ለመግባት ተገፋፍተዋል። በማንጋ ጉባኤ ውስጥ በዘወትር አቅኚነት የምታገለግለው ወጣቷ ኢዛቤል ይህን ግሩም የሆነ ንጹሕ አዳራሽ ከመመረቁ ከአንድ ቀን በፊት ከተመለከተች በኋላ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰንዝራለች፦ “እኔ በበኩሌ በቤራ ከተማ ካሉት ሁሉ ይበልጥ የተዋበ ቦታ ይህ እንደሆነ ይሰማኛል። እዚህ መሆን በጣም ያስደስተኛል።” አዶ ኮስታ የተባለ አንድ ሚስዮናዊ በአካባቢው የሚገኙ ባለ ሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች ሐቀኞች እንደሆኑ ስለሚያውቁ በልዩ ትእዛዝ ከሌላ አገር የሚመጡ ዕቃዎችን በማስገባት ረገድ በጣም ይተባበሩ እንደ ነበር ገልጿል። ከዚያም “ምንም እንኳ ብዙ የደከምን ቢሆንም የዚህ ሥራ ፍሬ ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ መሆኑን በማየታችን ተደስተናል” ሲል አክሏል።

አሁን አንድ የቤራ ከተማ ነዋሪ በወዳጅነት ቀርቦ “ታዲያ ቤተ ክርስቲያናችሁ የት ነው?” ብሎ ቢጠይቃቸው ምሥክሮቹ ከተሠሩት አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች ወደ አንዱ በመጠቆም “በዓለም አቀፉ ጎዳና በሚገኘው አቬኒዳ አኮርዱ ደ ሉሳካ፣ በፎርዝ እስኳድሮን ፖሊስ ጣቢያ በስተቀኝ ልታገኘው ትችላለህ” ብለው ሊመልሱ ይችላሉ። ከዚያም አንድ እርማት በማከል “ሆኖም ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን የመንግሥት አዳራሽ ነው!” ይሉታል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አፍሪካ

ሞዛምቢክ

ማፑቶ

ቤራ

[ምንጭ]

ካርታ፦ Mountain High Maps® Copyright ©1995 Digital Wisdom, Inc.

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ