ለጦርነት ተጠያቂው ማን ነው?
የሰው ልጆች ላደረጓቸው ጦርነቶች ተጠያቂው አምላክ ነውን? “አይደለም፣ አምላክ ጦርነት አይፈልግም።” ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንዳበቃ ለዚህ ጥያቄ እንዲህ ብለው መልስ የሰጡት ታዋቂው የጀርመን ፕሮቴስታንት ቄስ ማርቲን ኒመለር ናቸው። እኚህ ሰው የሰጡት አስተያየት በ1946 አቤቱ አምላክ ሆይ፣ ከሰማይ ተመልከት— ስድስት ስብከትa በተባለው መጽሐፍ (ጀርመንኛ) ላይ ታትሞ ወጣ። መጽሐፉ እንዲህ ይላል:-
“ለደረሱት [ጦርነቶች] አምላክን ተጠያቂ ለማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የአምላክን ቃል አያውቅም ወይም ለማወቅ አይፈልግም። እርግጥ ነው በተከታታይ ለደረሱት ጦርነቶች እኛ ክርስቲያኖች በአብዛኛው ተጠያቂ የመሆናችን ወይም ያለመሆናችን ጉዳይ ሌላ ነገር ነው። ያም ሆነ ይህ ከዚህ ጥያቄ በቀላሉ ልናመልጥ አንችልም። . . . አብያተ ክርስቲያናት ለረዥም ዘመናት ጦርነቶችን፣ ወታደሮችንና የጦር መሣሪያዎችን ለመባረክ በተደጋጋሚ ጊዜያት ራሳቸውን ማቅረባቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። እንዲሁም በጦርነት ጊዜያት ጠላቶቻቸው እንዲወድሙላቸው ክርስቲያናዊ ባልሆነ መንገድ ጸልየዋል። ይህ ሁሉ የእኛና የቀድሞ አባቶቻችን ስህተት እንጂ በፍጹም አምላክን ተጠያቂ አያደርገውም። በአሁኑ ጊዜ ያለነው ክርስቲያኖች በጦርነት ለመካፈልና ሰዎችን ለመግደል እምቢ በማለታቸው ምክንያት በመቶና በሺህ የሚቆጠሩ በማጎሪያ ካምፖች በተጣሉና [ከዚህም አልፎ] በተገደሉት ቅን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች [የይሖዋ ምሥክሮች] ተብለው በሚጠሩት ፊት ከፍተኛ ሐፍረት ይሰማናል።”
ዛሬ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካቆመ ከ50 ዓመት ያህል በኋላ የኒመለር ቃላት ሰላም ወዳድ ለሆኑ ሰዎች አንድ ቁም ነገር ያስተላልፋሉ። አሕዛብ ላፈሰሱት ደም ተጠያቂው አምላክ አይደለም! እንዲያውም አምላክ በዓለም ላይ ካለው ግጭት ገለልተኛ በሆኑት እውነተኛ አገልጋዮቹ በኩል ጦርነት ፈጽሞ እንደሚወገድ እያስነገረ ነው።— መዝሙር 46:9፤ ዮሐንስ 17:16
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የማርቲን ኒመለር ስብከት ከጊዜ በኋላ ጥፋተኝነትና ተስፋ በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታትሟል። ይሁን እንጂ የእንግሊዝኛው ትርጉም ከዋናው የጀርመንኛ ጽሑፍ ልዩነት ስላለው ይህ ጥቅስ የተተረጎመው ቀጥታ ከጀርመንኛው ጽሑፍ ነው።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
USAF photo