ሁሉም መለኮታዊ ሐሳብ የያዙ ናቸውን?
መጽሐፍ ቅዱስ እንዲጻፍ ሰዎችን ያነሳሳው የአምላክ መንፈስ አንዳንዶች እንደ ቅዱስ አድርገው የሚመለከቷቸው ሌሎች መጻሕፍትም እንዲጻፉ እገዛ አድርጓልን? (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህን ጥያቄ ያቀረበው “በቫቲካን መንግሥት የበላይ ተቆጣጣሪነት” ስለሚታተም ካቶሊኮች የታመነ ምንጭ እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱት አንድ የኢጣሊያ ኢየሱሳውያን መጽሔት (ላ ቺቪልታ ካቶሊካ) ነው።
የኢየሱሳውያኑ መጽሔት “እግዚአብሔር ከአይሁድና ከክርስቲያን እምነት ውጭ ያሉ እምነቶች በሚጠቀሙባቸው አንዳንድ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ እንኳን ሳይቀር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የቃሉ ዘር እንዲበተን አድርጓል” በማለት ይገልጻል። በኢየሱሳውያን አመለካከት መሠረት እንደ ዞሮአስትሪያን አቬስታ ወይም አራቱ የኮንፊሺየስ መጻሕፍት የመሳሰሉት “ቅዱሳን” መጻሕፍት የተጻፉት “እንዲያው ያለ ምንም የመንፈስ ቅዱስ ግፊት አይደለም፤ ስለዚህ ቢያንስ በተወሰነ መጠን ‘መለኮታዊ ሐሳቦችን’ ይዘዋል።”
ሆኖም ይህ ጽሑፍ ሌላ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጣል። “እንደነዚህ ያሉት ቅዱሳን መጻሕፍት የያዙት ሐሳብ ሁሉ የአምላክ ቃል ነው ማለት አይደለም” ሲል ከገለጸ በኋላ “በወቅቱ ተስፋፍቶ የነበረው በብዙ አማልክት የማመን ልማድ ወይም የፍልስፍና አስተሳሰብ እነዚህን መጻሕፍት በጻፉት ሰዎች ላይ ጎጂ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል” በማለት አክሎ ያብራራል። ላ ሬፑብሊካ የተባለው የኢጣሊያ ጋዜጣ የቫቲካን ዘጋቢ የሆነው ማርኮ ፖሊቲ እንደሚለው ከሆነ አንዳንድ ሌሎች ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲጻፉ መንፈስ ቅዱስ የተወሰነ አስተዋጽዖ አድርጓል የሚለው እምነት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና በታላላቅ ታሪካዊ ሃይማኖቶች መካከል ወዳጃዊ ግንኙነት ለመፍጠር በር ይከፍታል። ቀደም ሲል ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። እንዲያውም ዳግማዊ ዮሐንስ ጳውሎስ ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት በ1986 በአሲሲ ተደርጎ እንደነበረው የተለያዩ ሃይማኖቶች አንድ ላይ ተሰብስበው መጸለይ ይችላሉ።
ይሖዋ የሁከትና የዝብርቅ አምላክ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 14:33) ስለሆነም የእሱ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል እነዚህን የእርሱ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ መጻሕፍት ሌላው ቀርቶ የተወሰነ ክፍላቸው እንኳ ቢሆን እንዲጻፍ እገዛ አድርጓል ብለን በፍጹም ልንደመድም አንችልም። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ የተለያዩ ሃይማኖቶች የተለያዩ “ሃይማኖታዊ ወጎቻቸውን” አንድ ላይ እንዲያስተባብሩ ከማበረታታት ይልቅ ‘አንድ ተስፋ . . . አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንድ ጥምቀት’ እንዳለ ጽፏል።— ኤፌሶን 4:4, 5
ለዚህ ‘አንድ ተስፋ’ መሠረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ማመን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” በማለት በማያሻማ ሁኔታ ይገልጻል። (ሥራ 4:12) የአምላክን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ ኢየሱስ ዋነኛ መሣሪያ እንደሆነ አድርጎ የሚገልጽ ሌላ “ቅዱስ መጽሐፍ” የለም። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ ከተቀበልን ብቻ ነው ቃሉ ስለ ይሖዋ አምላክ ፍቅራዊ የመዳን ዝግጅት ሊያስተምረን የሚችለው።— ዮሐንስ 17:3፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13