የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ለሁሉም ዓይነት ሰዎች እውነትን ማዳረስ
ሐዋርያው ጳውሎስ ቀናተኛ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ ነበር። የሌሎች ተቃውሞ ‘ወንጌል’ የመስበክ ተልኮዕውን ከማከናወን እንዲያግደው አልፈቀደም። (1 ቆሮንቶስ 9:16፤ ሥራ 13:50-52) ጳውሎስ ሌሎችም የእሱን አርዓያ እንዲከተሉ አጥብቆ መክሯል።— 1 ቆሮንቶስ 11:1
የይሖዋ ምሥክሮች ለመስበክ በሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት በዓለም ዙሪያ የታወቁ ናቸው። አምላክ የሰጣቸውን ‘ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ’ ለማከናወን “አመቺ በሆነ ወቅትም” ሆነ “አስቸጋሪ በሆነ ወቅት” ለሌሎች ከመናገር ወደኋላ አይሉም። (2 ጢሞቴዎስ 4:2 NW፤ ማቴዎስ 28:19, 20) ቀጥሎ ያሉት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ተቃውሞ ባለባቸው አገሮች እንኳ ሳይቀር ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው በጣም አስፈላጊ መልእክት ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች እየተዳረሰ ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በታገደባት በምዕራባዊ ሰላማዊ ውቅያኖስ በምትገኝ አንዲት ደሴት የሚኖር አንድ የ12 ዓመት ልጅ በትምህርት ቤት በመጥፎ ባልንጀሮች እንደተከበበ ተገነዘበ። አብዛኞቹ የክፍሉ ተማሪዎች ሁልጊዜ ሲጋራ ያጨሳሉ፣ የብልግና ጽሑፎችን ያነባሉ፣ አስተማሪዎችን ያስቸግራሉ እንዲሁም ይደባደባሉ። ሁኔታው በጣም እየከፋ ስለሄደ ልጁ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት መዛወር ይችል እንደሆነ አባቱን ጠየቀ። ሆኖም አባትዬው በአካባቢው በሚገኙ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ያሉት ተማሪዎችም ጠባይ ከዚህ የተሻለ እንዳልሆነ ስለተሰማው በልጁ ሐሳብ ሳይስማማ ቀረ። ይሁን እንጂ ልጁን የረዳው እንዴት ነው?
አባትዬው ለወጣቶች የሚሆን አንድ መጽሐፍ እቤት እንዳለ ትዝ አለው። ይህ መጽሐፍ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ አንድ ዘመዱ የተሰጠው ስጦታ ነበር። መጽሐፉን ፈልጎ ካገኘው በኋላ ለልጁ ሰጠው። የመጽሐፉ ርዕስ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የሚል ነው።a ልጁ “የእኩዮችን ግፊት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” የሚለው ምዕራፍ ይበልጥ እንደሚረዳው ተገነዘበ። ይህ ምዕራፍ ክብርን ጠብቆ መኖር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወደ መጥፎ አካሄድ ዞር እንዲል ለመገፋፋት በሚሞክሩበት ጊዜ ግብዣቸውን እንዴት በዘዴ እምቢ ሊል እንደሚችል ጭምር አስተምሮታል። በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙትን ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ በማዋል ይህ ወጣት የእኩዮችን ግፊት እንዴት በተሳካ ሁኔታ መቋቋም እንደሚቻል አውቋል።
አባትዬው ልጁ ያሳያቸውን እነዚህንና ሌሎች አዎንታዊ ለውጦች በማስተዋል መጽሐፉን ለማንበብ ወሰነ። መጽሐፉ በያዛቸው በጣም ጠቃሚ ምክሮች ስለተማረከ አባትዬው የይሖዋ ምሥክሮችን የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመሩለት ጠየቀ። ቆየት ብሎ ሌሎች የቤተሰቡ አባላት አብረውት ያጠኑ ጀመር። ውጤቱስ ምን ሆነ? ልጁ፣ ታናሽ ወንድሙ፣ አባቱና ሁለት የልጆቹ አያቶች ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።
በዚሁ አገር ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ በመከተላቸው ታሰሩ። ይሁን እንጂ ያሉበት ሁኔታ ስለ አምላክ መንግሥት በድፍረት ከመናገር አላገዳቸውም። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የጌታ ራት ለማክበር የወኅኒ ቤቱን አዛዥ ፈቃድ ጠየቁ፤ ከዚያም እዚያው እስር ቤቱ ውስጥ እንዲያከብሩ ተፈቀደላቸው። 14 እስረኞች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፍላጎት እንዳላቸው ከመግለጻቸውም በላይ ይህን በጣም አስፈላጊ የሆነ በዓል አብረዋቸው በማክበራቸው እነዚህ ምሥክሮች በጣም ተደሰቱ! ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ ከእስር ቤት እንደተፈቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ቀጥለዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች ከ25 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ እገዳ ተጥሎባቸዋል አሊያም የተለያየ ተቃውሞ ወይም ስደት ይደርስባቸዋል። ይሁን እንጂ ልክ እንደ ሐዋርያት ‘ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ የሚናገረውን የምሥራች በትጋት ማስተማራቸውንና መስበካቸውን’ ገፍተውበታል።— ሥራ 5:42
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠመቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።