በግሪክ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሌላ ድል ተቀዳጁ
ጥቅምት 6, 1995 ሦስት አባላት ያሉት የአቴንስ ፍርድ ቤት ሸንጎ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሆኑ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮችን የሚመለከት አንድ ክስ አዳምጧል። ክሱ ሃይማኖት ማስቀየርን የሚያግደውን ሕግ ጥሰዋል የሚል ሲሆን አንድ የፖሊስ መኮንን ክሱን የመሠረተባቸው እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቱ ሄደው ካነጋገሩት በኋላ ነበር።
የመሐል ዳኛው ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ለማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳዩ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ሲሉ ጠይቀው ነበር:- “ይህን ሥራ ለምን ያህል ጊዜ ስትሠሩ ቆይታችኋል? በእነዚህ ዓመታት ሰዎች እንዴት ተመለከቷችሁ? በዚህ ጊዜ ለሥራችሁ ምን ዓይነት ምላሽ አግኝታችኋል? ከቤት ወደ ቤት ስትሄዱ ሰዎችን ምን ብላችሁ ታነጋግሯቸዋላችሁ?” በፍርድ ቤቱ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ሁሉ የተሰጠውን ጥሩ ምሥክርነት በትኩረት አዳምጠዋል።
አቃቤ ሕጉ እንኳ ሳይቀር እነሱን በመደገፍ መናገሩ የይሖዋ ምሥክሮቹን በጣም አስገርሟቸዋል። አቃቤ ሕጉ ንግግሩን ሲያጠቃልል የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝሯል:- “የይሖዋ ምሥክሮች አምላካቸውን ለማመንና ለማምለክ ብቻ ሳይሆን እምነታቸውን ከቤት ወደ ቤት፣ በሕዝብ አደባባዮችና በየመንገዱ የማስፋፋት፣ ከፈለጉም ጽሑፎቻቸውን በነፃ የማሰራጨት ሕገ መንግሥታዊ መብት አላቸው።” አቃቤ ሕጉ ፍርድ ቤቶችና የመንግሥት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የይሖዋ ምሥክሮችን በነፃ በመልቀቅ ያስተላለፏቸውን የተለያዩ ውሳኔዎች ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ለይሖዋ ምሥክሮች የፈረደበትን የኮኪናኪስ ቪ ግሪስ ጉዳይ ጠቅሷል።a “የግሪክ መንግሥት ለዚህ ክስ ካሳ ሳይቀር እንደከፈለ አትዘንጉ” ሲሉ አቃቤ ሕጉ አስጠንቅቋል። “ስለዚህ እነዚህን ጉዳዮች እንድንመለከት ስንጠየቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። እንዲያውም እነዚህ ክሶች መጀመሪያውኑ ፍርድ ቤት መቅረብ የለባቸውም።”
ከአቃቤ ሕጉ ንግግር በኋላ የይሖዋ ምሥክሮቹ ያቆሙት ጠበቃ ብዙም የሚናገረው ነገር አልነበረውም። ሆኖም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ሃይማኖት ማስቀየርን የሚከለክለው ሕግ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ከመሆኑም በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በግሪክ መንግሥት ላይ ውግዘት ሲያስከትል እንደቆየ ጠበቅ አድርጎ ገልጿል።
የመሐል ዳኛው ሁለቱን ዳኛዎች አየት አደረጉና ወንድምና እህት በነፃ እንዲለቀቁ ባንድ ድምፅ ተወሰነ። አንድ ሰዓት ከአሥር የፈጀው የፍርድ ጉዳይ ለይሖዋ ስምና ለሕዝቦቹ ድል ነበር።
የኮኪናኪስ ጉዳይ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከተደመጠ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት ማስቀየርን በተመለከተ ከቀረቡባቸው ክሶች በነፃ ሲለቀቁ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በግሪክ ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከስብከት ጋር የተያያዙ ችግሮች እየጠፉ በመሆናቸውና ምንም እንቅፋት ሳያጋጥማቸው ሥራቸውን ለመቀጠል በመቻላቸው ተደስተዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]