ሲኦልን በተመለከተ ያለው እውነታ
ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የእምነት መግለጫ የተገኘ አንድ ዘገባ ሲኦል የሚያመለክተው እሳታማ ምድጃን ሳይሆን ከሕልውና ውጪ መሆንን ነው ብሏል። “እዚህ ለውጥ ላይ ለመድረስ ያነሳሱ ብዙ ምክንያቶች አሉ” በማለት ዘገባው ያብራራል። “ይሁን እንጂ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል ከክርስትና እምነት ውስጥም ሆነ ከክርስትና ውጪ በሚያስፈራራ ሃይማኖት ላይ ሥነ ምግባራዊ ተቃውሞ ማጋጠሙና በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለዘላለማዊ ሥቃይ ስለሚዳርግ አምላክ የሚናገረው ፅንሰ ሐሳብ በክርስቶስ አማካኝነት ከተገለጸው ፍቅር ጋር ፈጽሞ እንደሚጻረር ብዙ ሰዎች እየተገነዘቡ መሆናቸው ይገኝበታል።”
ስለ ሲኦል ያለው ባህላዊ አመለካከት ችግር የፈጠረባት የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ብቻ አይደለችም። በተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የታቀፉ ሰዎችም ኃጢአተኞችን በእሳት የሚያቃጥል ተበቃይ አምላክ ማምለክ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። “ሰዎች ሞቅ ያለ የመውደድ ስሜት ያለውና ለስላሳ የሆነ አምላክ ይፈልጋሉ” በማለት የደክ ዩኒቨርሲቲ መለኮታዊ ትምህርት ቤት የሃይማኖትና የኅብረተሰብ ፕሮፌሰር የሆኑት ጃክሰን ካረል ተናግረዋል። “ኃጢአትንና ጥፋተኛነትን አስመልክቶ መናገር ከዘመናዊው አስተሳሰብ ጋር የሚቃረን ነው።”
የይሖዋ ምሥክሮች ከረጅም ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ሲኦል የሞቱ ሰዎች ተራ መቃብር እንጂ እሳታማ የሆነ መሠቃያ ቦታ እንዳልሆነ ሲያምኑ ቆይተዋል። ይህን አመለካከት የያዙት ብዙ ሰዎች ስለሚያምኑበት ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ “ሙታን ግን አንዳች አያውቁም። . . . በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና” ስለሚል ነው።— መክብብ 9:5, 10
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል ስለ ሙታን ሁኔታ እንዲህ ዓይነቱ ግልጽ ግንዛቤ ስለ ነበረው በ1896 እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእምነትና የግጥም መጻሕፍት እንዲሁም ብዙ ሰባኪዎች በስሕተት እንደሚያስተምሩት ያለ ዘላለማዊ መሠቃያ ቦታ የሚባል ነገር [በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ] አላገኘንም። ሆኖም በአዳም ኃጢአት ምክንያት የእኛ ዘር በሙሉ የተፈረደበትና በጌታ ሞት የተቤዠበት ‘ሲኦል፣’ ሺኦል፣ ሔድስ አግኝተናል፤ ይህ ‘ሲኦል’ መቃብር ሲሆን ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ ያመለክታል።”
በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ከአንድ መቶ ዓመት በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሲኦል የሚገልጸውን እውነት አስተምረዋል።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቻርልስ ቲ ራስል