በፈረንሳይ ውስጥ ለተሰነዘሩት የሐሰት ክሶች ምላሽ መስጠት
በቅርቡ በፈረንሳይ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሐሰት ክሶች ውርጅብኝ ዒላማ ሆነው ነበር። በአውሮፓና በጃፓን በሃይማኖት ኑፋቄዎች ምክንያት የተከሰቱትን አሳዛኝ ሁኔታዎች አስታከው የመገናኛ ብዙሃን የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ የተዛቡ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅና በጣም አደገኛ ከሆኑት ኑፋቄዎች መካከል አንዱ ናቸው ተብሎ በሐሰት ተነገረ።
እነዚህን ጉዳዮች ለማስተካከል ሲሉ የይሖዋ ምሥክሮች እነማን ናቸው? ክርስቲያኖች ናቸው? የሕክምና አገልግሎት ይቀበላሉ? ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የሚሰብኩት ለምንድን ነው? ለሥራቸው የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክሮች ኅበረተሰቡን የሚጠቅሙት እንዴት ነው? እንደሚሉት ላሉት ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ አንድ ትራክት የይሖዋ ምሥክሮች አሳተሙ።
በፈረንሳይኛ የወጣው ይህ ትምህርት ሰጪ ትራክት የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ማወቅ የሚያስፈልግዎት ጉዳይ የሚል ርዕስ ነበረው። ትራክቱን የተቻለውን ያህል ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ሲባል አንድ ዘመቻ ተቀናጀ። ከግንቦት 13 እስከ ሰኔ 9, 1996 ባለው ጊዜ ውስጥ ከዘጠኝ ሚልዮን የሚበልጡ ቅጂዎች ተሰራጩ።
ይህ ትራክት የሕዝብ ባለ ሥልጣናትን ጨምሮ የብዙዎችን ስሜት ነክቷል። አንድ የክልል ምክር ቤት አባል ትራክቱን ካነበቡ በኋላ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተሰነዘረው ትችት በጣም አስቆጥቶኛል። ሥራችሁ የበጎ አድራጎት ተግባር እንደሆነና ለሌሎች ጥቅም ተብሎ እንደሚደረግ በተደጋጋሚ ጊዜያት ልገነዘብ ችያለሁ።” አንድ የአውሮፓ ፓርላማ አባል ለትራክቱ ምላሽ ሲሰጡ “አብዛኞቹ ሰዎች እናንተ እንዳላችሁበት ባለ የክርስቲያኖች ቡድንና በኑፋቄዎች መካከል ያለውን ልዩነት አሳምረው ያውቃሉ” ሲሉ ጽፈዋል።
በብሪታኒ አንድ የይሖዋ ምሥክር ለአንድ ቄስ ትራክቱን እንዲወስዱ ሲጋብዛቸው ቄሱ ሳያቅማሙ ተቀበሉት። “ስለምታደርጉት ነገር ላመሰግናችሁ እፈልጋለሁ” ሲሉ ቄሱ ተናግረዋል። ከዚያም እንዲህ ሲሉ ቀጠሉ:- “እኔ ያለሁበት ቤተ ክርስቲያን አባሎችን ወደ ቤታቸው አስገብተው ሻይ ቡና እንዲሏችሁ አበረታታቸዋለሁ። በአገልግሎታችሁ ላይ ለምታገኟቸው እኔ ቤት እንደነበራችሁ ልትነግሯቸው ትችላላችሁ። በተጨማሪም ጽሑፎቻችሁን ማንበብ እንደሚያስደስተኝ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።”
በአልዛስ የሚኖር አንድ የፕሮቴስታንት አማኝ ትራክቱን ካገኘ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት በመጠየቅ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጻፈ። “በቤተ ክርስቲያኔ ላይ የነበረኝ እምነት ሁሉ ስለጠፋ መንፈሳዊነቴን በአዲስ መልኩ ለመጀመር ጓጉቼአለሁ” ሲል ጽፏል። በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የምድር ክፍሎች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንድ ጊዜ የሐሰት ክሶች ቢሰነዘሩባቸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን የአምላክ ዓላማዎች ሰዎች በትክክል እንዲያውቁ መርዳታቸውን ይቀጥላሉ።— 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17