ለ403 ዓመታት የቆየው ጋብቻ አደጋ ላይ ወደቀ
በስዊድን ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ከ400 ዓመታት በላይ ጥብቅ ወዳጅነት መሥርተው ይኖሩ ነበር። አሁን ግን በሃይማኖትና በመንግሥት መካከል ያለው ቅርርብ እየተዳከመ መጥቷል።
የሉተራን ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ሃይማኖት የሆነው በ1593 ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሁሉም ስዊድናውያን የተጠመቁ አባላት መሆን ነበረባቸው። ከብዙ ዓመታት በኋላ በ1850ዎቹ አንድ ማስተካከያ ተደረገ። ስዊድናውያን መጠመቅ እንደማያስፈልጋቸው ተገለጸ። ሆኖም የሉተራን ቤተ ክርስቲያን አባላት እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ነበር። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመደገፍና የምታከናውነውን የሲቪል አገልግሎት ወጪ ለመሸፈን ቀረጥ ከከፈሉበት ገቢያቸው ውስጥ 1 በመቶ እንዲከፍሉ ይፈለግባቸው ነበር። በቅርቡ ደግሞ ሌላ ለውጥ ተከስቷል። ከ1952 ጀምሮ ስዊድናውያን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከቤተ ክርስቲያኗ መውጣትና አብዛኛውን የቤተ ክርስቲያኒቷን ቀረጥ ከመክፈል ነፃ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን በስዊድን የነበራትን የበላይነት እያጣች ነው። አይሁድን፣ ካቶሊክንና እስልምናን ጨምሮ ስዊድን ከሚኖሩት ሰዎች መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ሉተራውያን ያልሆኑ ስደተኞች በመሆናቸው ይህ ሁኔታ መከሰቱ የማይቀር ነው። ከዚህም የተነሳ በ1996 መግቢያ ላይ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን አባላት 86 በመቶ ብቻ ነበሩ። ይህም ቁጥር ቢሆን እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ነው።
እየጨመረ የመጣው የግዴለሽነት ዝንባሌ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት እያሰፋ ነው። ንጉሡ የግድ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን እንደሌለበት፣ የሉተራን ተከታይ የሆኑ ወላጆች የሚወልዷቸው ልጆች ወዲያውኑ የመንግሥት ቤተ ክርስቲያን የሆነው የሉተራን ቤተ ክርስቲያን አባላት ሆነው መታየት እንደማያስፈልጋቸው በይፋ የተነገረው ቀደም ብሎ ነበር። ከዚህም በላይ ዘ ዳላስ ሞርኒንግ ኒውስ በ2000 ዓመት “የአገሪቱ አድባራትና መንግሥት ግምገማ አድርገው ከፍተኛ መጠን ያለውን ሃብት መከፋፈል አለባቸው። ቤተ ክርስቲያኗ በአብዛኛው ከቀረጥ የምታገኘውንና ለዓመት የምትመድበውን $1.68 ቢልዮን የአሜረካ ዶላር ባጀት መቀነስ አለባት” ብሏል። ከ2000 ዓመት በኋላ ቤተ ክርስቲያኗ የራሷን ቀሳውስት ትሾማለች።
የግዴለሽነት ዝንባሌ መስፋፋትና የአባላት መመናመን ሕዝበ ክርስትናን እያጠቃት ባለበት በአሁኑ ወቅት በስዊድን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እያደጉ መሄዳቸውን ቀጥለዋል። የ1997 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ በዚህች አገር 24, 487 የአምላክ መንግሥት አስፋፊዎች አንዳሉና 10 በመቶ የሚሆኑት የሙሉ ጊዜ አቅኚ ሆነው በመስበክ ላይ መሆናቸውን ዘግቧል። ከእነዚህም መካከል ብዙዎቹ ከፍ ያለ የአገልገሎት መብት ላይ ለመድረስ እየተጣጣሩ ነው። ለምሳሌ ያህል በ1995 በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጊልያድ ትምህርት ቤት ሰልጥነው ሚስዮናዊ ሆነው ለማገልገል 20 ባልና ሚስት ማመልከቻ አስገብተዋል። በዚያን ወቅት 75 ስዊድናውያን ቀደም ባሉት ክፍሎች ተመርቀው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሚስዮናዊ ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ። የእነርሱ ግሩም አርአያነት፣ የሚልኳቸው የሚያበረታቱ ደብዳቤዎችና የሚያደርጓቸው ጉብኝቶች ይህን ታላቅ መብት ለመጨበጥ የሚጓጉትን እንዳነቃቋቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
በሚልዮን የሚቆጠሩ የሕዝበ ክርስትና አባላት ሞራል እየወደቀ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ግን “ከልባቸው ደስታ የተነሳ ይዘምራሉ።”— ኢሳይያስ 65:13, 14
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ስዊድን