እንዲህ ዓይነቱን ሁኔታ የማናይበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
በአሁኑ ጊዜ በሄድንበት ሁሉ የምናየው ውጥረት፣ ግጭትና ጦርነት የሚያሳዩ ምስሎችን ነው። ይሁን እንጂ የዚህ መጽሔት ዓላማ ከዚህ ቀደም ከየአቅጣጫው የሰማኸውን መጥፎ ዜና ማስተጋባት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ይህ ልዩ እትም ቢያንስ ከሁለት የሚያጽናኑ እውነቶች ጋር ያስተዋውቅሃል። አንደኛው እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ጥንታዊ ትንቢቶቸ በዘመናችን ስለሚሰሙት አስደንጋጭ ዜናዎች አስቀድመው መግለጻቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ይኸው የትንቢት መጽሐፍ ራሱ በዚህ ገጽ ላይ ያለው ስዕል የሚያሳየውን ዓይነት ነገሮች የሚወገዱበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጽ መሆኑ ነው። ጦርነት ጨርሶ አይኖርም። የቦምብ ድብደባ፣ የደፈጣ አደጋ ጣዮች፣ የተጠመዱ ቦንቦች ወይም የአሸባሪነት ጥቃት ፈጽሞ አይኖሩም። የችግር አለንጋ የሚገርፋቸው የሙት ልጆች ወይም ቤት የሌላቸው ስደተኞች አይኖሩም። እውነተኛና ልብን የሚያሳርፍ ሰላም የሰፈነበት ዓለም ይሆናል። እንዲህ ያለውን ጊዜ ለማየት ትጓጓለህን? ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ነገር እንድትመረምር እናበረታታሃለን። ከምትገምተው በላይም መጽናኛ ልታገኝበት ትችላለህ።