“ለጌታ ለክርስቶስ ባሪያ ሁኑ”
በታሪክ ዘመናት ሁሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በባርነት ቀንበር ሲሰቃዩ ኖረዋል። ለምሳሌ ያህል ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት እስራኤላውያን በግብፃውያን አሠሪዎቻቸው ከፍተኛ ሥቃይ ደርሶባቸው ነበር። ጡብ እንዲሠሩ ለማድረግ “በብርቱ ሥራ ያስጨንቁአቸው ዘንድ ግብፃውያን ጨካኞች የሆኑ አሠሪዎችን ሾሙባቸው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።— ዘጸአት 1:11 የ1980 ትርጉም
በዛሬው ጊዜ በብዙዎቹ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ቃል በቃል ባሪያዎች ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ብዙዎች አንዳንድ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ሳይቀር ለረዥም ሰዓታት ለመሥራት ይገደዳሉ። የገንዘብ ባሪያ በሚባለው በከባድ ሸክም ውስጥ ወድቀዋል።
ይሁን እንጂ ከባድ ያልሆነ ሌላ ዓይነት ባርነት አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ እርሱ አማኝ የሆኑትን “ለጌታ ለክርስቶስ ባሪያ ሁኑ” በማለት አሳስቧቸዋል። (ቆላስይስ 3:24 NW) የክርስቶስ ባሪያ ለመሆን የመረጡ ሁሉ ካለባቸው ከባድ ሸክም ተላቀው እረፍት ያገኛሉ። ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ብሏል:- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”—ማቴዎስ 11:28-30
አንድ ሰው የክርስቶስን ቀንበር መሸከሙ ካለበት ለቤተሰቡ ቁሳዊ ነገሮች የማቅረብ ግዴታ ነፃ አያደርገውም። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ከዚህ ይልቅ ቁሳዊ ሀብት በማሳደድ ከሚመጡ የተለያዩ ጠንቆች ነፃ ያደርገዋል። ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ ቁሳዊ ሀብት ማካበትን ዋነኛ ግባቸው ከማድረግ ይልቅ መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች ይረካሉ።— 1 ጢሞቴዎስ 6:6-10፤ ከ1 ቆሮንቶስ 7:31 ጋር አወዳድር።
በተጨማሪም ክርስቲያኖች የአምላክን መንግሥት “ምሥራች” የመስበክ ኃላፊነታቸውን ሙሉ በሙሉ በመፈጸም እረፍት ያገኛሉ። (ማቴዎስ 24:14) ይህም እውነተኛ ደስታና እርካታ ያመጣል!
“ለጌታ ለክርስቶስ ባሪያ” መሆን በመቻላችን አመስጋኞች መሆን ይገባናል!
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.