የከኔቲከት ከፍተኛ ፍርድ ቤት የበሽተኛዋን መብት አስከበረ
ሚያዝያ 16, 1996 የከኔቲከት ዩ ኤስ ኤ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክሮች ደም አንወስድም የማለት መብታቸውን አስከበረ። ይህ ውሳኔ ቀደም ሲል በአንድ የአውራጃ ፍርድ ቤት የተላለፈውን ብያኔ የሚሽር ነበር።
ኔሊ ቬጋ የተባለች አንዲት የይሐዋ ምሥክር ነሐሴ 1994 የመጀመሪያ ልጅዋን ከተገላገለች በኋላ በጣም ብዙ ደም ይፈሳት ጀመር። ይህን የደም መፍሰስ ለማስቆም የተደረገው ጥረት ምንም ውጤት አላስገኘም። የወ/ሮ ቬጋ ሁኔታ እየተባባሰ ሲመጣ ሆስፒታሉ ደም ለመስጠት እንዲችል የፍርድ ቤት ትእዛዝ ለማግኘት ፈለገ። ቀደም ሲል ወ/ሮ ቬጋ ሆስፒታል በምትቆይባቸው ጊዜያት ምንም ዓይነት ደም ወይም የደም ተዋፅኦ እንደማትወስድ የሚገልጽና ይህ ውሳኔዋ ከሚያስከትልባት ነገር ሆስፒታሉን ከኃላፊነት ነፃ የሚያደርግ የሕክምና ሰነድ ፈርማ ነበር። የሆኖ ሆኖ ሆስፒታሉ ደም አስገድዶ መስጠቱ እናቱን ከሚፈልገው አዲስ ከተወለደው ሕፃን ፍላጎት ጋር የሚስማማ ነው ሲል ተከራከረ። ፍርድ ቤቱን ያሳሰበው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ወ/ሮ ቬጋ ከደም ማነስ በስተቀር ወጣትና ጤነኛ መሆኗ ነበር። ስለዚህ ምንም እንኳ ባልዋና ጠበቃዋ ቢቃወሙም በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ መሠረት ደም እንድትወስድ ተደረገ።
ከጊዜ በኋላ ጉዳዩ በከኔቲከት ለሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረበ። እዚያም ሆስፒታሉ የወሰደው እርምጃ የወ/ሮ ቬጋን መብት የጣሰ መሆኑን በአንድ ድምፅ ወሰነ። የተላለፈው ውሳኔ እንደሚከተለው ይላል:- “ጉዳዩ በአውራጃው ፍርድ ቤት የተሰማው እኩለ ሌሊት ላይ ሲሆን በሁለቱም ወገኖች የነበሩት ሰዎች ሙሉ መረጃ ለማቅረብ በማይችሉበት በጣም ጥድፊያ ባለበት ሁኔታ ስር ነበር።”
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ይህ ውሳኔ የይሖዋ ምሥክሮች ላልሆኑ ሌሎች ሰዎችም የጎላ ትርጉም አለው። የወ/ሮ ቬጋ ጠበቃ የሆኑት ዶናልድ ቲ ሪድሊ “ውሳኔው ከሐኪሞቻቸው ውሳኔ ጋር ለማይስማሙ በሽተኞች በሙሉ ጠቃሚ ነው። ውሳኔው ከአሁን በኋላ ሆስፒታሎች በሽተኞችን በማስገደድ ሃይማኖታዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ያልሆነ የሥነ ምግባር አቋማቸውን እንዲያፈርሱ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ያደርጋቸዋል” ብለዋል።