አረጋውያንን የገጠማቸው ችግር
የ68 ዓመት አዛውንት የሆኑት እማማ ኦኒያን ምዕራብ አፍሪካ በሚገኝ አንድ ትልቅ ከተማ ይኖራሉ። ገና ወጣት በነበሩበት ጊዜ ሲያረጁ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው አጠገባቸው ሆነው ሲጦሯቸው በዓይነ ሕሊናቸው ይታያቸው ነበር። አሁን ግን ሐሩር ፀሐይ ላይ ቁጭ ብለው ቀዝቃዛ ውኃ ሲሸጡ ይውላሉ። የሚያገኟት ጥቂት ገቢ ሕይወታቸውን ለማቆየት ትረዳቸዋለች። ሁለት ልጆቻቸው በሌላ ሩቅ አገር ይኖራሉ። ገንዘብ ከላኩላቸው ረዥም ጊዜያት ተቆጥረዋል።
የዛሬን አያድርገውና ድሮ፣ በአፍሪካ አረጋውያን ከፍተኛ አክብሮት ይሰጣቸው ነበር። ጥበብና ማስተዋል በሰጧቸው ዕድሜ በቸራቸው ተሞክሮና እውቀት ይከበሩ ነበር። የልጅ ልጆችን በማሳደግ እርዳታ ያበረክቱ ነበር። ወጣቶች ምክርና ሐሳብ ለማግኘት ወደ እነርሱ ይሄዱ ነበር። ሰዎች “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም [አሮጊቷንም] አክብር” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር ያከብሩ ነበር።—ዘሌዋውያን 19:32
ጊዜው ተለውጧል። ድህነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነትና ወደ ከተሞች የሚደረገው ፍልሰት ብዙ አረጋውያን ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ አስገድዷቸዋል። ሄልፕኤጅ ኬንያ የተባለው ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ካሚለስ ዌር “አረጋውያንን የመጦርና የመንከባከብ ባህል በከፍተኛ ፍጥነት እየተዳከመ መጥቷል” በማለት ተናግረዋል።
እርግጥ የቤተሰብ ትስስር እየተዳከመ የመጣው በአፍሪካ ውስጥ ብቻ አይደለም። ጋርዲያን ዊክሊ ጃፓንን አስመልክቶ እንደሚከተለው በማለት ዘግቧል:- “በኮንፊሺያኒዝም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የጃፓኖች ጥሩ ሥነ ምግባር ዋነኛ መሠረት የነበረው ወላጆችን የመጦር ኃላፊነት በከተማ ኑሮ እየተዳከመ ሄዷል። በአሁኑ ጊዜ 85 በመቶ የሚሆኑት ጃፓናውያን የሚሞቱት በሆስፒታል ውስጥ ወይም በአረጋውያን መጦሪያ ቦታ እያሉ ነው።”
ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ከልባቸው አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ ለወላጆቻቸው አክብሮት ለመስጠት ይጣጣራሉ። “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ። (ኤፌሶን 6:2, 3) አረጋውያን ወላጆችን ማክበርም ሆነ መጦር ሁልጊዜ ቀላል ነገር ባይሆንም እንኳ የተትረፈረፈ ወሮታ ሊያስገኝ ይችላል።