ልትተማመኑ የምትችሉት ማን በሰጠው ተስፋ ላይ ነው?
ሰባ አራት አባላት ያሉት አንድ የማኅበራዊ ተንታኞች ቡድን በ1893 በቺካጎ በተደረገ የዓለም ትርእይት ላይ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለመወያየት ተሰብስቦ ነበር። (ቦታው ከላይ የሚታየው ነው።) ከ100 ዓመታት በኋላ ማለትም በ1993 ይፈጸማሉ ብለው ከተነበዩአቸው ነገሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:- “ብዙ ሰዎች ለ150 ዓመታት መኖር ይችላሉ።” “የእስር ቤቶች ቁጥር ይቀንሳል እንዲሁም ፍቺ የማያስፈልግ ነገር እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።” “እውነተኛ እድገት ሁልጊዜ ቀላል የሆነ አሠራርን ወደ መከተል ስለሚያዘነብል መንግሥታዊ አስተዳደር ያልተወሳሰበ ይሆናል።”
በተመሳሳይም በ1967 ዘ ይር ቱታውዘንድ የተባለ አንድ መጽሐፍ እንደሚከተለው በማለት ተንብዮ ነበር:- “በ2000 ዓመት ኮምፒዩተሮች ይበልጥ ሰው የሚያስመስላቸውን ምናልባትም ውብ የሆነን ነገር የማድነቅንና የፈጠራ ችሎታን ጨምሮ ‘የሰውን የማሰብ ችሎታ’ ለመተካከል፣ ለመኮረጅ ወይም በልጠው ለመሄድ ይችላሉ።” “በ2000 ዓመት በመጠነኛ ዋጋ የሚሸጡና አብዛኛውን የቤት ውስጥ ሥራ የሚያከናውኑ ሮቦቶች . . . ይኖራሉ ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል።”
የሰው ልጅ ወደፊት ስለሚፈጸመው ነገር ለመተንበይ አለመቻሉ አምላክ በዚህ ረገድ ካለው ችሎታ ጋር በጣም ይለያያል። ለምሳሌ ያህል ከላይ ያሉትን ትንበያዎች መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ያለንበትን ጊዜ አስመልክቶ ከ2000 ዓመታት ገደማ በፊት ከተናገረው ጋር አወዳድር። “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹን ቀናት’ አስመልክቶ የተናገረው ይህ ትንቢት በጊዜያችን ፍጻሜያቸውን ካገኙት ትንቢቶች መካከል አንዱ ብቻ ነው። የአምላክ ቃል የኢየሱስ የመገኘቱ “ምልክት” ጦርነትን፣ የምግብ እጥረትን፣ ቸነፈርን፣ የመሬት መንቀጥቀጥንና የአምላክ መንግሥት ምሥራች በዓለም ዙሪያ መሰበክን እንደሚጨምር አስቀድሞ ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:3-14፤ ሉቃስ 21:11
አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ሳይፈጸሙ የማይቀሩ መሆናቸው አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ከብዙ ዘመናት በፊት እንደሚከተለው በማለት እንዲጽፍ አነሳስቶታል:- “እናንተም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል፤ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም።”—ኢያሱ 23:14
አዎን፣ አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች በሙሉ በቅርቡ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። የአምላክ መንግሥት ሕመምን፣ ወንጀልን፣ የአደንዛዥ ዕፅ ሱስን፣ ረሃብንና ጦርነትን ታስወግዳለች፤ መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። (መዝሙር 37:10, 11, 29፤ ራእይ 21:3, 4) ይህ ትንቢት ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጸም ልትተማመኑ ትችላላችሁ! ትንቢቱን የተናገረው ‘ሊዋሽ የማይችለው’ ፈጣሪያችን ነው።—ቲቶ 1:2፤ ከዕብራውያን 6:13-19 ጋር አወዳድር።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Cleveland State University Archive