“ጥልቅ ውኃዎችን” መቅዳት
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ምክር በሰው ልብ እንደ ጠሊቅ ውኃ ነው፤ አእምሮ [“ማስተዋል፣” NW] ያለው ሰው ግን ይቀዳዋል” በማለት ይገልጻል። (ምሳሌ 20:5) ዛሬ በብዙ አገሮች ውኃ መቅዳት ከባድ ሥራ ቢሆንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይበልጥ አድካሚ ነበር። ኢየሱስ ሳምራዊቷን ሴት ባነጋገራት ጊዜ 23 ሜትር ጥልቀት ካለው የያዕቆብ ጉድጓድ ውኃ እየቀዳች ነበር!—ዮሐንስ 4:5-15
ምሳሌ 20:5 እንዳመለከተው በአንድ ሰው ልብ ውስጥ ያሉትን ጥልቅ ሐሳቦችና ስሜቶች ለማግኘት የሚያስፈልገው ማስተዋል ከአንድ ጉድጓድ ውኃ ለመቅዳት ከሚያስፈልገው ጥረት ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ በአብዛኛው የሕይወት መስክ እውነት ነው። ለምሳሌ ያህል በረዥም ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ዕውቀትና ተሞክሮ ያካበቱ ግለሰቦች ሳታውቅ አትቀርም። እነዚህ ሰዎች ሳይጠየቁ በራሳቸው አነሳሽነት ምክር የመስጠት ዝንባሌ ከሌላቸው ምክሮቹን ማውጣጣት ያስፈልግህ ይሆናል። ጉጉት ስታሳይ፣ ጥያቄዎች ስትጠይቅና በዘዴ ስትመረምር መቅጃህን ጥልቅ ወደሆነ የጥበብ ጉድጓድ ውስጥ የሰደድህ ያህል ነው።
በምሳሌ 20:5 ላይ ያለው ምክር በቤተሰብ ውስጥም ይሠራል። ብዙ ጊዜ ሚስቶች “ባሌ ስሜቶቹን አይገልጽልኝም!” ሲሉ ተሰምተዋል። ምናልባትም አንድ ባል “ሚስቴ እኔን ማነጋገር አቁማለች!” ይል ይሆናል። በእንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሥር በትዳር ጓደኛ ልብ ውስጥ ተሰውረው ያሉትን ሐሳቦች ለማውጣት ማስተዋል ያስፈልጋል። በዘዴ የሚቀርቡ ጥያቄዎች (በቀኑ ውስጥ ችግሮች ገጥመውህ/ሽ ነበር? ምን ገጠመህ/ሽ? እንዴት ልረዳህ/ሽ እችላለሁ?) አብዛኛውን ጊዜ በልባቸው ውስጥ ያለውን ሐሳብ አውጥተው እንዲነጋገሩ ያስችሏቸዋል። ይህን የመሰለ ማስተዋል ማሳየት ለባልና ሚስቱ ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ የትዳርን ሰንሰለት ያጠናክራል።