ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ትናፍቃለህን?
ሦስት ተራዳና ደርብ ያላት አንዲት ከእንጨት የተሠራች መርከብ ባሁኑ ስያሜው ኬፕ ኮድ ማሳቹሴትስ ዩ ኤስ ኤ ወደብ ደረሰች። የመርከቧ ሠራተኞችና 101 የሚሆኑት ተሳፋሪዎች ለ66 ቀናት በባሕር ላይ ስለተጓዙ ደክሟቸዋል። አትላንቲክ ውቅያኖስን ለማቋረጥ በጣም ከባድና አስቸጋሪ ጉዞ ያደረጉት ከሃይማኖታዊ ስደትና ከኢኮኖሚ ችግር ለመሸሽ ነው።
ሜይፍላወር የተባለችው የዚህች መርከብ መንገደኞች፣ ከብዙ ቀናት ጉዞ በኋላ ኅዳር 11, 1620 ለመጀመሪያ ጊዜ የብስ በማየታቸው እንደ አዲስ የሚጀምሩትን ሕይወት በማሰብ ፊታቸው በደስታ ፈካ። በመርከቧ ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ ጎልማሳ ወንዶች የሜይፍላወር ስምምነትን በመፈራረም የተሻለ ዓለም ለመገንባት መሠረት ጣሉ። በስምምነቱ ውስጥ “በአጠቃላይ ለመንደሩ ነዋሪዎች ጥቅም በማሰብ” “ፍትሐዊና አድልዎ የሌለባቸው ሕግጋት” ለመደንገግ ተስማሙ። በሥነ ምግባር የታነጸና ለሁሉም ተስማሚ የሆነ ፍትህ የሰፈነበት ዓለም እውን ሆኗልን?
ምንም እንኳን መርከቧ ላይ የተፈረመው ስምምነት ለአሜሪካ የአስተዳደር ሥርዓት እንደ አንድ የመሠረት ድንጋይ ቢቆጠርም በዓለም ዙሪያ እንደሚከሰተው ሁሉ በአሜሪካም የፍትሕ መጓደል የተለመደ ክስተት ነው። ለምሳሌ ያህል ከሰረቀና የሱቁን ባለቤት በጥይት ከመታ በኋላ ሊያመልጥ ሲሞክር በፖሊስ በጥይት የተመታውን ሰው ጉዳይ እንውሰድ። ፖሊሱንና የኒው ዮርክ ከተማ አስተዳደርን በመክሰስ በሚልዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ካሳ በማግኘት በክሱ ረትቷል።
ሌላም ምሳሌ ተመልከት። በካሊፎርኒያ ፓሳዴና የሚገኙ የሕግ ተማሪዎች የጥብቅና ሙያ ፈተና እየወሰዱ ሳለ ከመሃላቸው አንዱ በድንገት ይታመምና ራሱን ይስታል። ወዲያው በአጠገቡ የነበሩ ሁለት ተማሪዎች የሕክምና ባለሙያዎች እስኪመጡ ድረስ የልቡ ምትና እስትንፋስ እንዲቀጥል በማድረግ ሕይወቱ እንዳያልፍ ረዱት። እርሱን በመርዳት 40 ደቂቃ አባከኑ። ፈተናውን ለመጨረስ የማካካሻ ሰዓት በጠየቁ ጊዜ ፈተናውን ያካሂድ የነበረው ኃላፊ ጥያቄያቸውን ውድቅ አደረገባቸው።
ለወንጀል ድርጊቶች የሚሰጠውም ቅጣት ሌላው ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ነው። የኢኮኖሚ ተንታኝ የሆኑት ኤድ ሩበንስታይን እንደጠቆሙት:- “አብዛኞቹ ወንጀለኞች አይያዙም። ከሚያዙትም መካከል አብዛኞቹ ሕግ ፊት አይቀርቡም። ብዙ ወንጀለኞች ቃላቸውን ብቻ ሰጥተው ይለቀቃሉ። አብዛኛውን ጊዜ ወንጀለኛው የጠበቀውን ያህል ቅጣት አይደርስበትም።” ሩበንስታይን ቤት ሰርስሮ የመስረቅን ወንጀል አኃዛዊ መረጃዎች ሲመረምሩ አንድ ቤት ሰርሳሪ ሌባ “ከፈጸማቸው ወንጀሎች ብዛት አንፃር ሲታይ ከ98 በመቶ በላይ ከመታሰር እንደሚያመልጥ” ደርሰውበታል። ከቅጣት የማምለጡ አጋጣሚ ሰፊ መሆኑ የወንጀሎችና የወንጀል ሰለባዎች ቁጥር ከፍ እንዲል አድርጓል።—መክብብ 8:11
በብዙ አገሮች ጥቂት የሆኑ ቱጃሮች ይበልጥ እየበለጸጉ ሲሄዱ በአንፃሩ ድሃው ሕዝብ በኢኮኖሚ ይበልጥ እየደቀቀ ይሄዳል። ሰዎች በቆዳቸው ቀለም፣ በዘራቸው፣ በቋንቋቸው፣ በጾታቸው ወይም በሃይማኖታቸው ምክንያት ኑሯቸውን ማሻሻል ይባስ ብሎም፣ የዕለት ጉርስ ማግኘት አስቸጋሪ በሚሆንባቸው ጊዜ ይህ ዓይነቱ የፍትሕ መጓደል ይበልጥ ጉልህ ሆኖ ይታያል። ለምሳሌ ያህል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው “የሂንዱ እምነት በተንሰራፋበት በደቡብ እስያ ከአንድ ቢልዮን ሰዎች መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት፣ በአብዛኛው በሕንድና በኔፓል የሚኖሩ ናቸው፣ ከልደታቸው እስከሞታቸው ድረስ ከሰው ተገልለው ይኖራሉ።” ከዚህም የተነሳ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት፣ በረሃብና በበሽታ ይጠፋሉ። ከልደት እስከ ሞት በሕይወታቸው ሙሉ በደል ይደርስባቸዋል።
ከሰዎች ቁጥጥር ውጭ ስለሚመስሉት የፍትህ መጓደሎችስ ምን ለማለት ይቻላል? በተፈጥሮ ታውረው፣ አእምሮአቸው ደካማ ሆኖ ወይም አካለ ስንኩል ሆነው ስለሚወለዱ ልጆችም እስቲ አስቡ? በአጠገብዋ ያሉ ሴቶች ጤናማ ሕፃናት ታቅፈው እሷ ግን አካለ ስንኩል የሆነ ልጅ ወይም ሙት ሽል የወለደች ሴት ፍትህ እንደተጓደለባት ሆኖ አይሰማትምን?
የፍትሕ መጓደልና ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚመጡት እንደ ከፍተኛ ሰቆቃ እንዲሁም ሰላም፣ ደስታና እርካታ ማጣት ያሉት መዘዞች መበራከታቸው ያሳዝናል። በሚያዩት ወይም በደረሰባቸው በደል በመቆጣት ብዙ ሰዎች ወደ ዓመፅ ዘወር ማለታቸው የሰው ልጆችን መከራ ከማባባስ በስተቀር ምንም አልፈየዱም። አብዛኞቹ ጦርነቶች የተካሄዱት በደል ደርሶብኛል በሚል ምክንያት ነው።
የሰው ልጅ ፍትህ የሰፈነበት ዓለም ማስገኘት የተሳነው ለምንድን ነው? ይህ ዓይነቱ ዓለም እንዲያው ሕልም ብቻ ነውን?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ምንጭ]
Corbis-Bettmann
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሜይፍላወርን ስምምነት ሲፈራረሙ
[ምንጭ]
Corbis-Bettmann