ድምፅ ሳያሰሙ ፈጣሪያቸውን ያወድሳሉ
የፀሐይ መጥለቅ እጅግ ማራኪ የሆነ ተፈጥሮአዊ ክስተት ነው። ሆኖም በኢጣሊያ ቱስካኒ ከሚገኙት የአፑና ሰንሰለታማ ተራራዎች ጀርባ የምትጠልቀው ፀሐይ ዕይታ በዓይነቱ ልዩ ነው።
ከሩቅ ሲታይ ፀሐይዋ ከተራራው ጀርባ የምትጠልቅ ሳይሆን በቀጥታ ተራራው ውስጥ የወደቀች ይመስላል። ለምን? ምክንያቱም የተራራው ጫፍ ተቦርቡሮ የተሠራ የሚመስል ተፈጥሮአዊ ቅስት አለው። ከዚህ ቅስት የተነሳ ተራራው ሞንቴ ፎራቶ የሚል ስም ማትረፉ የተገባ ነው። የስሙም ትርጉም የተቀደደው ተራራ ማለት ነው። ምድር በፀሐይ ዙሪያ ስለምትዞር ፀሐይዋ ስትጠልቅ ሞንቴ ፎራቶ ቅስት ውስጥ የገባች መስላ የምትታየው በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው።
ልክ እንደ ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ ግዑዝ የሆኑት ሰማያትም ፈጣሪያቸውን ያወድሳሉ። እንዴት? አንድ የሚያምር ሥዕል ለሠዓሊው አድናቆትን እንደሚያተርፍለት ሁሉ ይህም ተመሳሳይ ነው። በሰማይ ላይ ያሉት አካላት ስለ ይሖዋ ኃይል፣ ጥበብና ግርማ በግልጽ ይናገራሉ። መዝሙራዊው ይህንን ሲገልጽ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል” ብሏል። (መዝሙር 19:1፤ 69:34) ፀሐይና ሌሎች ግዑዛን አካላት ፈጣሪያቸውን የሚያወድሱ ከሆነ እኛ ደግሞ እንዴት አብልጠን እርሱን ማወደስ ይኖርብናል!—መዝሙር 148:1, 3, 12, 13