“እስከ ዛሬ ከተዘጋጁት የአዲስ ኪዳን ኢንተርሊንየር ትርጉሞች ሁሉ የላቀ ነው”
ዶክተር ጄሰን ቤዱን የኪንግደም ኢንተርሊንየር የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉምን የገለጹት ከላይ እንዳለው በማለት ነበር። እንዲህ ሲሉም አብራርተዋል:-
“በብሉሚንግተን [ዩ ኤስ ኤ] በሚገኘው በኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖታዊ ጥናቶች ክፍል አንድ ኮርስ አስተምሬ መጨረሴ ነው . . . ኮርሱ በዋነኛነት የሚያተኩረው በወንጌሎች ላይ ነው። በኪንግደም ኢንተርሊንየር የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ቅጂዎች አማካኝነት የእናንተን ድጋፍ አግኝተናል። ተማሪዎቼ ለትምህርቱ ከተዘጋጁት የመማሪያ መጻሕፍት እንደ አንዱ አድርገው ተጠቅመውበታል። እነዚህ የኪንግደም ኢንተርሊንየር አነስተኛ ጥራዞች ለኮርሱ ከፍተኛ እገዛ ያበረከቱ ሲሆን በተማሪዎቼም ዘንድ በጣም ተወዳጅ ነበሩ።”
ዶክተር ቤዱን በኮሌጁ ውስጥ ለሰጡት ኮርስ በኪንግደም ኢንተርሊንየር የተጠቀሙት ለምንድን ነው? እንዲህ በማለት መልስ ሰጥተዋል:- “በአጭሩ እስከዛሬ ከተዘጋጁት የአዲስ ኪዳን ኢንተርሊንየር ትርጉሞች ሁሉ የላቀ ነው። ከጥቅሶቹና በጊዜያችን ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥናት ከሚያገለግሉት ጽሑፎች ጋር ትውውቅ ያለኝና በሙያው የሰለጠንሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ነኝ። በነገራችን ላይ የይሖዋ ምሥክሮች አባል አይደለሁም። ሆኖም ጥራት ያለው የጽሑፍ ሥራ ምን ዓይነት እንደሆነ አውቃለሁ፤ የእናንተ ‘የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ’ ድንቅ ሥራ ሠርቷል። ከግሪክኛው ጎን ለጎን ያስቀመጣችሁት የእንግሊዝኛ ትርጉም ፍጹም ትክክልና ወጥ ከመሆኑ የተነሳ አንባቢው ግሪክኛ ተናጋሪ በነበረው በዚያ ትውልድና በእኛ ዘመን መካከል ያለውን የቋንቋ፣ የባሕልና የግንዛቤ ልዩነት በግልጽ እንዲያስተውል የሚያስችል ነው። ‘የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም’ ለግሪክኛው ጽሑፍ ታማኝ በመሆን በዘልማድ ሲሰጡ የነበሩ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ሳይከተል ቃል በቃል የተተረጎመ ከፍተኛ ጥራት ያለው ሥራ ነው። በዛሬው ጊዜ ከሚሠራባቸው የተዋጣላቸው የትርጉም ሥራዎች በብዙ መንገዶች የሚልቅ ነው።”
የኪንግደም ኢንተርሊንየር የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ለአምላክ ቃል ፍቅር ያላቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ከተጻፈበት የግሪክኛው ጽሑፍ ጋር ለማስተዋወቅ ሲባል በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ነው። በስተግራ (በቢ ኤፍ ዌስትኮት እና በኤፍ ጄ ኤ ሆርት የተዘጋጀውን) ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ዚ ኦሪጅናል ግሪክ የተባለውን ትርጉም አስፍሯል። ከግሪክኛው ጽሑፍ ስር ቃል በቃል የሰፈረው የእንግሊዝኛው ጥሬ ፍቺ ይገኛል። በቀኝ በኩል ባለው ጠባብ ረድፍ ደግሞ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ይገኛል። ይህም የኢንተርሊንየሩን ትርጉም ከዘመናዊው የእንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጋር ለማነጻጸር ያስችላል።