አምላክ ዓለምን ያጠፋ ይሆን?
ሊቀ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል እንደተናገሩት ከሆነ የሰው ልጆች የወደፊቱን ጊዜ ያለ ሥጋት በትምክህት ሊጠባበቁ ይችላሉ። በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደታየው “ሰዎች ኃጢአት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል ምናልባትም የሚፈጽሙት ኃጢአት ከጥፋት ውኃ በፊት ከተፈጸመው የከፋ ሊሆን ይችላል” ብለው ተናግረዋል። ያም ሆኖ ግን “አምላክ ለኖኅ የገባው ቃል ኪዳን እንደሚያሳየው በአሁኑ ጊዜ እርሱ ራሱ የፈጠረውን ዓለም እንዲያጠፋ የሚያደርገው ምንም ኃጢአት እንደሌለ መገንዘብ እንችላለን” በማለት ሊቀ ጳጳሱ አብራርተዋል።
አምላክ ዓለምን በፍጹም አያጠፋም የሚለው ይህ አባባል እውነት ነውን? ከጥፋት ውኃ በኋላ አምላክ ኖኅን “ሥጋ ያለውም ሁሉ ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም” እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘፍጥረት 9:11) ሊቀ ጳጳሱ እንደሚሉት ከሆነ አምላክ “[ምድርን] እንደማያጠፋት ቃል ገብቷል።”
ፈጣሪ ፕላኔታችን እንድትጠፋ እንደማይፈቅድ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አስቀምጦታል። መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር . . . ለዘላለም ነው” በማለት ይናገራል። (መክብብ 1:4) ሆኖም ከጥፋት ውኃው የምንማረው ሊቀ ጳጳሱ ያልጠቀሱት አንድ ነገር አለ።
ኢየሱስ በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ በምድር ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች ‘በኖኅ ዘመን ከነበረው ሁኔታ’ ጋር እንደሚመሳሰሉ ተናግሯል። በዚያን ጊዜ ሰዎቹ ‘የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ አላወቁም’ ነበር። (ማቴዎስ 24:37-39) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘ያን ጊዜ የነበረው ዓለም በውኃ ሰጥሞ እንደ ጠፋ’ ሁሉ አሁን ባለውም ዓለም ላይ “እግዚአብሔርን የማያመልኩ ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ” ጥፋት እያንዣበበ መሆኑን ጽፏል።—2 ጴጥሮስ 3:5-7
ኢየሱስና ጴጥሮስ አምላክ ከኖኅ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ዘንግተውታልን? በፍጹም አልዘነጉትም! አምላክ ለኖኅ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ይህን ክፉ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው ለማምጣት በጥፋት ውኃ አይጠቀምም። ከዚህ ይልቅ “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ” በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ክንድ ይጠቀማል። (ራእይ [አፖካሊፕስ] 19:11-21) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ምድር አትጠፋም ክፉ የሆነው የሰው ዘር “ዓለም” ግን ያለምንም ጥርጥር ተጠራርጎ ይጠፋል። (ምሳሌ 2:21, 22፤ ራእይ 11:18) ከዚያ በኋላ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29