ዶክተሮች፣ ዳኞችና የይሖዋ ምሥክሮች
በመጋቢት 1995 የይሖዋ ምሥክሮች በብራዚል ሁለት ትምህርታዊ ሴሚናሮችን አድርገው ነበር። የሴሚናሮቹ ዓላማ ምን ነበር? ሆስፒታል የገባው ታካሚ የይሖዋ ምሥክር በሚሆንበት ጊዜ ደም ስለማይወስድ የሕክምናና የሕግ ባለሙያዎችን ትብብር ለማግኘት ሲባል ነው።—ሥራ 15:29
በአንዳንድ አጋጣሚዎች ዶክተሮች ምሥክር የሆኑ ታካሚዎችን ፍላጎት ችላ በማለት አስገድደው ደም ለመስጠት የሚያስችላቸውን የፍርድ ቤት ትእዛዝ ለማግኘት መሞከራቸው የሚያሳዝን ነው። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ምሥክሮቹ ራሳቸውን ለመጠበቅ ያለውን ሕጋዊ መንገድ ሁሉ ተጠቅመዋል። የሆነ ሆኖ ከግጭት ይልቅ ትብብር ይመርጣሉ። በመሆኑም ተመሳሳይ ዓይነት ደም በመስጠት ከማከም ይልቅ ብዙ ዓይነት አማራጮች እንዳሉና የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን አማራጮች በደስታ እንደሚቀበሉ ትምህርታዊ ሴሚናሮቹ አጉልተዋል።a
የሳኦ ፓውሎ የሕክምና ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ላይ ድሮውንም የምሥክሮቹን አቋም ደግፎ ነበር። በጥር 1995 ምክር ቤቱ፣ ዶክተሩ ባዘዘው ሕክምና ላይ ተቃውሞ ካለ ታካሚው ሕክምናውን ላለመቀበልና ሌላ ዶክተር ለመምረጥ ነፃነት አለው በማለት ወስኖ ነበር።
በአሁኑ ወቅት በታካሚው ፍላጎት መሠረት ያለ ደም ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕክምና ባለሙያዎች በብራዚል የሕክምና ማኅበረሰብ ውስጥ መኖራቸው የሚያስመሰግን ነው። በመጋቢት 1995 ከተካሄዱት ትምህርታዊ ሴሚናሮች ወዲህ በብራዚል ውስጥ በዶክተሮች፣ በዳኞችና በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለው ትብብር በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሏል። በብራዚል የሚታተመው አምቢቱ ኦስፒታላር የተባለው የሕክምና መጽሔት የይሖዋ ምሥክሮች ደምን በተመለከተ ያላቸው አቋም እንዲከበርላቸው በጽኑ የሚደግፍ ርዕስ በ1997 አሳትሟል። የሪዮ ዲ ጄኔሮና ሳኦ ፓውሎ ግዛቶች የክልሉ የሕክምና ምክር ቤት ባሰፈረው መሠረት “ዶክተሩ የበሽተኛውን ሕይወት ለማትረፍ ያለበት ኃላፊነት የታካሚውን የሕክምና ምርጫ ለማስከበር ካለበት ኃላፊነት የበለጠ እንደሆነ ተደርጎ መታየት የለበትም።” በአሁኑ ጊዜ ይህ በሰፊው የታወቀ ሆኗል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? የተባለውን ብሮሹር ተመልከት።