እርስዎስ ለምን በስብሰባዎች ላይ አይገኙም?
ባለፈው ዓመት የ73 ዓመቱ አዛውንት ኤንጃኡኩአ ኡሊምባ 450 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው መንገድ ተጉዟል። ይህንን ሁሉ ርቀት የተጓዘው በእግሩ ሲሆን 16 ቀን ፈጅቶበታል።
አዛውንቱ ይህንን ረጅም ጉዞ ያደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ከሚያደርጓቸው ዓመታዊ የአውራጃ ስብሰባዎች በአንዱ ለመገኘት ነበር። በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ከመጠን በላይ ተደስቶና መንፈሳዊ ጥንካሬ አግኝቶ እንደገና የ16 ቀን ጉዞ በማድረግ ወደ ቤቱ ተመልሷል። ይሁን እንጂ ስብሰባው ይህን ያህል ጥረት ሊደረግለት የሚገባ ነበርን? አዎን፣ ነበር! ኤንጃኡኩአ ኡሊምባ ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ በየዓመቱ እንዲህ ዓይነት ጉዞ ሲያደርግ ቆይቷል።
ባለፈው ዓመት በ230 አገሮች በተደረጉ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባዎች ከተገኙት 15 ሚልዮን ሰዎች መሐል ይህ አፍሪካዊ ሰው አንዱ ነበረ። በእርግጥ አብዛኞቹ በአውራጃ ስብሰባው ላይ ለመገኘት ብዙ ቀናት በእግራቸው መጓዝ አላስፈለጋቸውም። አብዛኞቹ ወደስብሰባው ቦታ የመጡት በመኪና፣ በአውቶቡስ፣ በባቡር ወይም በአውሮፕላን ነው። እርስዎስ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተው ነበርን?
በ1998ም በዓለም ዙሪያ የአውራጃ ስብሰባዎች የሚደረጉ ሲሆን ስብሰባው በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የሚካሄደው በበጋ ወቅት ይሆናል። ኤንጃኡኩአ ኡሊምባ ጤንነቱ ከፈቀደለት በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ተመሳሳይ ረጅም ጉዞ ያደርግ ይሆናል። ይህ አዛውንትም ሆነ ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ ፕሮግራም ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለው፣ እምነትን የሚያጠነክርና ኃይል የሚያድስ ትምህርት ያገኛሉ። በስብሰባው ላይ ለተገኙ ሁሉ ዓመቱን ሙሉ የሚያስታውሱት ጊዜ ይሆንላቸዋል። እርስዎም እንዲገኙ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልዎታለን። በአካባቢዎ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በአቅራቢያዎ የሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ የት እንደሚከናወን ሊነግሩዎ ፈቃደኞች ናቸው።