መልካም ምግባር ያስመሰግናል
በኢጣሊያ የሚታተመው ላ ጋዜታ ዴል ሜዞጆርኖ የተባለው ጋዜጣ የይሖዋ ምሥክሮች “ማቴራ፣ ድንቅ የዋሻ ቤቶች የሞሉባት ከተማ” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ በማውጣታቸው አመስግኖ ነበር። ይህ ርዕስ የወጣው በብዙ ቋንቋዎች ሰፊ ስርጭት ባለው በሐምሌ 8, 1997 ንቁ! መጽሔት ላይ ነበር። ንቁ! በአሁኑ ጊዜ በ81 ቋንቋዎች የሚታተም ሲሆን በዓለም ዙሪያ ከ19 ሚልዮን በሚበልጡ ቅጂዎች ይሰራጫል። ጋዜጣው “[የማቴራንን] ከተማ ታሪካዊና ስነ ጥበባዊ ቅርስ ለሕዝብ በማሳወቅ ረገድ” የንቁ! መጽሔት በዚህ የበጋ ወቅት አቻ የማይገኝለት ሥራ አከናውኗል ሲል ገልጿል።
ጋዜጣው በ1997 በማቴራ ተካሂዶ የነበረውን “በአምላክ ቃል ማመን” የተባለውን የአውራጃ ስብሰባ አስመልክቶ ምሥክሮቹን አወድሷል። ጋዜጣው ምሥክሮቹ ስላከናወኑት ተግባር ሲናገር “በበጋ ወር በሐሩር የፀሐይ ወቅት ላይ 4,000 የሚያክሉ ሰዎች [ከተማው ውስጥ በሚገኘው] በሴቴምብሬ 21 ስታዲየም እንዲሰበሰቡ ለማድረግ ገንዘብ ሳይከፈላቸው ለማጽዳት፣ ቀለም ለመቀባትና ይህን የስፖርት ማዕከል (በተለይም መጸዳጃ ቤቶቹን) የተሻለ ለማድረግ ብዙ ደክመዋል፤ ለዚህ ስብሰባ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ለመግዛት ከራሳቸው ኪስ ወጪ አድርገዋል” ብሏል።
የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ጎረቤቶች ለመሆን ይጥራሉ። (ማቴዎስ 22:37-39) እንዲሁም “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ . . . በሚጐበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ይከተላሉ።—1 ጴጥሮስ 2:12