አነጋገርህ የሚያቆስል ነው ወይስ የሚፈውስ?
በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ብዙዎች ‘ልባቸው የተሰበረና መንፈሳቸው የደቀቀ’ መሆኑ እምብዛም አያስገርምም። (መዝሙር 34:18 የ1980 ትርጉም) በመሆኑም ‘የተጨነቁትን ነፍሳት በሚያጽናና ቃል ለመናገርና ደካሞችን ለመደገፍ’ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ያሳያሉ። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) ሆኖም አንድ የእምነት አጋራችን ቢያስቀይመን ወይም ከባድ ስህተት ቢፈጽምብንስ? እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ግለሰቡን ለመገሰጽ እንደምንችል ሆኖ ይሰማን ይሆናል። ይሁን እንጂ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። አንድ ምክር የቱንም ያህል ጠቃሚ ቢሆን ሸካራ በሆነ መንገድ ከተሰጠ ጎጂ ሊሆን ይችላል። ምሳሌ 12:18 “እንደሚዋጋ ሰይፍ የሚለፈልፍ ሰው አለ” ይላል።
ስለዚህ እርማት ለመስጠት ወይም አለመግባባትን ለመፍታት በምናስብበት ጊዜ የምሳሌ 12:18ን ሁለተኛ ክፍል ማስታወሱ አስፈላጊ ነው:- “የጠቢባን ምላስ ግን ጤና ነው።” ሁልጊዜ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ምክር የሚያስፈልገኝ ከሆነ፣ እኔ በምን ዓይነት መንገድ እንድመከር እፈልጋለሁ?’ አብዛኞቻችን ጥሩ ምላሽ የምንሰጠው ለነቀፋ ሳይሆን ለማበረታቻ ነው። ስለዚህ ለማመስገን ንቁ ሁን። ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ የበደለን ሰው መሻሻል እንዲያደርግ የሚያነሣሣው ሲሆን የተሰጠውን ማንኛውንም እርዳታ በአመስጋኝነት ሊቀበል ይችላል።
የምንናገራቸውን ቃላት በየዋህነት ማለዘባችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ፈዋሽ ቃላት ምክር ተቀባዩ መዝሙራዊው ቀጥሎ ያለውን ሲጽፍ የተሰማው ዓይነት ስሜት እንዲሰማው ያደርጋሉ:- “ጻድቅ በምሕረት ይገስጸኝ፣ ይዝለፈኝም፣ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ።”—መዝሙር 141:5