የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በትሕትና ራስን ከይሖዋ መንገድ ጋር አስማምቶ መኖር
“የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ።” ዕብራዊው ነቢይ ሶፎንያስ ከ26 መቶ ዓመታት በፊት ያሰማው ይህ ጥሪ በዛሬው ጊዜም በምድር ዙሪያ ለሚኖሩ ሰዎች እየቀረበ ነው። (ሶፎንያስ 2:3) ይሖዋን መፈለግ ሲባል ምን ማለት ነው? የመጀመሪያው እርምጃ እርሱ ብቻ እውነተኛና ሕያው ስለሆነው አምላክ ስለ ይሖዋ የሚገልጸውን እውቀት መቅሰም ነው።—ኤርምያስ 10:10፤ ዮሐንስ 17:3
ሆኖም እውቀት ማግኘት በራሱ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ወደ ማግኘት አያደርስም። አንድ ሰው የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለገ ይህን እውቀት በሥራ ላይ ማዋል አለበት። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ከሱሪናም የተገኘው ቀጥሎ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው አስተሳሰቡንና ባሕሪውን ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር በትሕትና አስማምቶ በመኖር ነው።—ኤፌሶን 4:22-24
ዕድሜው በ30ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ የሚገኘው ኤዲ የተባለ መምህር፣ ‘አሁን ባለው ኅብረተሰብ ውስጥ ሃይማኖት የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው?’ እና ‘በጣም ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው መጽሐፍ ቅዱስ ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር ይስማማል?’ ለሚሉት ጥያቄዎቹ አጥጋቢ መልሶች ለማግኘት ይፈልግ ነበር። ኤዲ የይሖዋ ምሥክሮች ቤቱ መጥተው ሲያነጋግሩትና ለእነዚህ ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልስ ሲሰጡት በጥሞና አዳመጠ። ምሥክሮቹ የሰጡት ማብራሪያ ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ሲል ማስታወሻም ያዘ።
ኤዲ ከዚህ በፊት አባል በነበረበት ሃይማኖት አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ከጦጣ ተሻሽለው እንዲመጡ በማድረግ ነው የሚል ትምህርት ተምሯል። ይህም በመሆኑ ምሥክሮቹ ሕይወት እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? የተባለውን መጽሐፍ ሲሰጡት ያለ አንዳች ማንገራገር ተቀበለ። መጽሐፉ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ታሪክ የሚሰጠው ግልጽ ማብራሪያ በጣም አስደነቀው። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ አማካኝነት እውነትን እንዳገኘ አረጋገጠ!
ሆኖም አንድ ፈተና ገጠመው። ከኤዲ ጋር በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች በስርቆትና በማጭበርበር ድርጊት የተጠላለፉ ነበሩ። ይህም በመሆኑ በፊቱ ሁለት ምርጫዎች ተደቀኑ:- አብረውት የሚኖሩ ጓደኞቹ የሚከተሉትን የተበላሸ አኗኗር መቀበል አለዚያ ደግሞ አምላክን የሚያስከብር አኗኗር ለመከተል ሲል ከእነሱ መራቅ ነበረበት። ኤዲ አምላካዊ አኗኗር ለመከተል በመወሰን ጥበብ የታከለበት ምርጫ አደረገ። የነበረውን ክፉ ባልንጀርነት እርግፍ አድርጎ በመተው ቤቱን ለቅቆ ወጣ።—1 ቆሮንቶስ 15:33, 34
ኤዲ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመረ በኋላ ፈጣን እድገት አደረገ። ከዚህም በተጨማሪ አለባበሱንና የፀጉር አያያዙን አስተካከለ። የተማረውን ነገር ለጓደኞቹና ለዘመዶቹ መንገር ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ‘ምሥራቹን’ ለሕዝብ በመስበኩ ሥራ ላይ የመካፈል መብት ሲያገኝ በጣም ተደሰተ። (ማቴዎስ 24:14፤ ሥራ 20:20) ታኅሣሥ 1996 በውኃ በመጠመቅ ራሱን ለይሖዋ መወሰኑን ሲያሳይ ለረዥም ጊዜ ሲጠባበቀው የነበረው ነገር ተሳካለት።
በየዓመቱ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ‘ይሖዋን እንዲፈልጉ’ ለሚቀርብላቸው ጥሪ ምላሽ ይሰጣሉ። እንዲህ በማድረጋቸውም “ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው” የሚለው የምሳሌ 22:4 አባባል ትክክል መሆኑን በሕይወታቸው ላይ ሲፈጸም ያያሉ። አዎን፣ እውነትን የሚያፈቅሩ ሰዎች በትሕትና ራሳቸውን ከይሖዋ መንገድ ጋር አስማምተው በመኖር በአሁኑ ጊዜ እነዚህን በረከቶች ከማግኘታቸውም በላይ ወደፊት በዚህችው ምድር ላይ የሚያገኟቸውን ዘላለማዊ በረከቶች በእርግጠኛነት ሊጠባበቁ ይችላሉ።—መዝሙር 37:29
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ካሪቢያን ባሕር
ሱሪናም
ጉያና
ፍሬንች ጉያና
ብራዚል
[ምንጭ]
ሉል:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.