“በሌሎች ዘንድ አድናቆት ያተረፈ” ሥራ
ሐዋርያው ጴጥሮስ መሰል ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል መክሯቸዋል:- “ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፣ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፣ . . . እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 2:12) በኢጣሊያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ ዓመታት ይህን የመሰለውን መልካም ባሕርይ በግልጽ ሲያሳዩ ኖረዋል። ኢየሱስ “በሰገነት ላይ ስበኩ” ሲል የሰጠው መመሪያ የያዘውን መንፈስ በማንጸባረቅ ከሕዝብ ዕይታ ሳይሰወሩ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን በይፋ ያካሂዳሉ። (ማቴዎስ 10:27፤ ዮሐንስ 18:20) በመሆኑም አንድ ኢጣሊያዊ ጠበቃና አንድ ቄስ የይሖዋ ምሥክሮች “አስመሳይ ሃይማኖታዊ ኑፋቄ” እንደሆኑና “ሰዎችን ከሚያጠምዱ ምሥጢራዊ ቡድኖች” አንዱ እንደሆኑ የሚገልጽ ጽሑፍ በማሳተም በወነጀሏቸው ጊዜ በእነዚህ ስም የሚያጠፉ መግለጫዎች የተነሳ ምሥክሮቹ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ወሰኑ።
በመጀመሪያው ችሎት ላይ ፍርድ ቤቱ ጠበቃውና ቄሱ ሕግ አልጣሱም የሚል ብያኔ አስተላለፈ። ይሁን እንጂ ሐምሌ 17, 1997 ላይ የቬኒስ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት የመጀመሪያው ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ብያኔ በመሻር ሁለቱም ተከሳሾች ጥፋተኞች መሆናቸውን አረጋገጠ። ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የተጠቀሱት ሁለቱም ጽሑፎች ‘የይሖዋ ምሥክሮች’ ሃይማኖት ተከታዮችን ስም ሊያጎድፉ የሚችሉ አባባሎችና መግለጫዎች ይዘዋል። የጽሑፎቹ ዓላማ ምሥክሮቹ በሕዝብ ዘንድ እንዲጠሉ ለማድረግ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነው።” ፍርድ ቤቱ እነዚህ ጽሑፎች “ለመዘገብም ሆነ ግምገማ ለመስጠት የተሰጠውን መብት ሕጋዊ በሆነ መንገድ አልተጠቀሙበትም” ሲል ገልጿል። ፍርድ ቤቱ ሁለቱ ስም አጥፊዎች መቀጮ እንዲከፍሉ የበየነባቸው ከመሆኑም በላይ በሁለቱም ክሶች ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ምሥክሮቹ ያወጡትን ወጪ ጨምሮ ለፍርድ ቤት የወጣውን ወጪ በሙሉ እንዲከፍሉ አዟል።
የቬኒስ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በጽሑፍ ባወጣው ብያኔ ላይ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ያለመቻቻል መንፈስንና ሃይማኖታዊ አክራሪነትን መከላከል የሚቻለው [የኢጣሊያ] ሕገ መንግሥት ያጸደቃቸው መብቶች በሁሉም ላይ እኩል ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው በማድረግና እነዚህን መብቶች ጠብቆ በማቆየት ብቻ ነው።” ውሳኔው የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ምሥጢራዊም ሆነ በሃይማኖት ስም በማስመሰል የሚደረግ አለመሆኑን ገልጿል። ፍርድ ቤቱ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል:- “ምሥክሮቹን ከምሥጢራዊ ቡድኖች ጋር መመደቡ የታሪክ ሐቅ የያዘውን መመዘኛ እንኳ ግምት ውስጥ የማያስገባ ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው ስለሚያስተምሩት ትምህርት ምንም ዓይነት አመለካከት ይኑረው ሃይማኖቱ በብዙ ከተማዎች ውስጥ የሚገኝና በተለይ ደግሞ በእሁድ ቀናት እንዲሁም በሌሎች የበዓል ቀናት አባላቱ በስፋት የሚያካሂዱት የስብከት እንቅስቃሴ በደንብ የሚታወቅ ከመሆኑም በላይ የሚያደርጉት ጥረት በሌሎች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈ ነው።” ይህም በመሆኑ በኢጣሊያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በቅንዓት በመስበክና ጥሩ አርአያ የሚሆን ምግባር በማሳየት ያስመዘገቡት ታሪክ በእነሱ ላይ የተቆሰቆሰው ጭፍን ጥላቻ እንዲወገድ አስተዋጽኦ አድርጓል።—ማቴዎስ 5:14-16፤ 1 ጴጥሮስ 2:15