በዘመናዊ ግሪክኛ የተዘጋጀ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ
ነሐሴ 23, 1997 በግሪክ “በአምላክ ቃል ማመን” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለተገኙት ተሰብሳቢዎች ልዩ ቀን ነበር። የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም መደምደሚያ ላይ የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የተባለ በዘመናዊ ግሪክኛ የተዘጋጀ አንድ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱ በማስታወቂያ ተነገረ። በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት የተዋጡት ተሰብሳቢዎች የደስታ ዕንባ እያነቡ ከመቀመጫቸው ተነስተው ለረዥም ጊዜ በማጨብጨብ የተሰማቸውን ደስታ ገለጹ!
ከ1905 ወዲህ ባሉት ጊዜያት የይሖዋ ምሥክሮች ሲጠቀሙ የነበረው በ19ኛው መቶ ዘመን አንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄስ ባዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነበር። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለረዥም ዓመታት ከፍተኛ ጥቅም ሲሰጥ ቆይቷል። ሆኖም ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ይበልጥ ትክክለኛና ለመረዳት ቀላል የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማግኘቱ አስፈላጊ መሆኑን ተረዱ። በ1993 በግሪክኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን የአዲሲቱ ዓለም የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ባገኙ ጊዜ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷቸው ነበር። አሁን ግን በዘመናዊው ግሪክኛ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በማግኘታቸው ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆኗል።
አንዲት የይሖዋ ምሥክር “የአምላክ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በገዛ ራሳችን ቋንቋ በቀላሉ መረዳት በምንችልበት መንገድ፣ በሚጥምና ለማንበብ በሚማርክ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ቀርቦልናል” ስትል የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምን በተመለከተ ከልብ የተሰማትን አድናቆት ገልጻለች። አንዳንዶቹ አዲሱን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂያቸውን ማንበብ የጀመሩት ገና ቤታቸው እንደደረሱ ነበር። ስሜቱ በጥልቅ የተነካ አንድ ተሰብሳቢ መላውን የኢዮብ መጽሐፍ አንብቦ እስኪጨርስ እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት ድረስ መጽሐፍ ቅዱሱን ከድኖ ማስቀመጥ አልቻለም ነበር!
ይህ በግሪክኛ ቋንቋ የተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ሰባት ዓመታት ያህል የፈጀ ትጋት የተሞላበት ሥራ ውጤት ነው። አንድ ደብዳቤ “ቀና ልብ ያላቸውን ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ ለመርዳት የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትልን ምንም አያጠራጥርም” በማለት ይገልጻል።