አሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመንን ያወደመ ጦርነት
1914
ዚ ኦርላንዶ ሴንቲኔል ለተባለ ጋዜጣ አምድ የሚጽፉት ቻርሊ ሪስ አዲሱን ሺህ ዓመት አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ከ1914–18 የተካሄደውና 19ኛው መቶ ዘመንን ያወደመው ጦርነት ገና አላበቃም።” ምን ማለታቸው ነበር? እንዲህ ሲሉ አብራርተዋል:- “ታሪክ በዘመናት ቀመር አይመራም። የእምነቶች፣ የግምቶች፣ የአመለካከቶችና የግብረ ገብነት ስብስብ የሰፈነበት ነበር የተባለለት 19ኛው መቶ ዘመን ያበቃው በጥር 1, 1901 ሳይሆን በ1914 ነበር። ተመሳሳይ ትርጉም የተሰጠው 20ኛው መቶ ዘመንም የጀመረው በዚሁ ጊዜ ነበር። . . .
“በሕይወት ዘመናችን በሙሉ ሲያስጨንቁን የኖሩት ግጭቶች በጠቅላላ ለማለት ይቻላል መነሻቸው ይህ ጦርነት ነበር። አብረውን የኖሩና ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ አብዛኞቹ ምሁራዊና ባህላዊ አስተሳሰቦች የመነጩት ከዚያ ጦርነት ነበር። . . .
“ጦርነቱ ይህን ያህል ጥፋት ሊያስከትል የቻለው ሰዎች የወደፊት ዕጣቸውን ለመቆጣጠር ይችላሉ የሚለውን የሕዝቦች እምነት በማጨለሙ ምክንያት ነው ብዬ አስባለሁ። . . . ጦርነቱ ሰዎች ይህን የተሳሳተ እምነት እንዲተዉ አድርጓቸዋል። በሁለቱም ወገን የነበሩ ሰዎች ጦርነቱ በዚህ መልክ ይደመደማል ብለው አላሰቡም ነበር። የብሪታንያንና የፈረንሳይን ግዛቶች አውድሟል። የብሪታንያ፣ የፈረንሳይና የጀርመን ሰዎችን ያቀፈ አንድ ሙሉ ምርጥ ትውልድ በጠቅላላ ገድሏል። . . . በአጭር ጊዜ ውስጥ 11 ሚልዮን ሰዎችን ገድሏል።”
የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ ‘የአሕዛብ ዘመን’ ብሎ የጠራው ጊዜ የሚያበቃበት ዓመት 1914 እንደሚሆን ከ120 ዓመታት በላይ ሲናገሩ ቆይተዋል። (ሉቃስ 21:24) ከሞት የተነሣውና ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ ክርስቶስ በዚያ ዓመት የሰማያዊው መንግሥት ንጉሥ በመሆን ዙፋን ላይ ተቀምጧል። በዚህ መንግሥት አማካኝነት ይሖዋ አምላክ ይህን መቶ ዘመን ለይተው ያሳወቁትን መከራዎች በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋል።—መዝሙር 37:10, 11፤ መክብብ 8:9፤ ራእይ 21:3, 4
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
U.S. National Archives photo