የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ምሥራቹን ከማወጅ ወደኋላ አትበሉ
አውሮፓውያን አሳሾች ለመጀመሪያ ጊዜ የቬነዙዌላን ባሕረ ሰላጤና የማራኪቦን ሐይቅ በጎበኙበት ወቅት በውኃው ዳርቻ ጥልቀት በሌለው ውኃ ውስጥ የተተከሉ ምሰሶዎች ላይ በተገነቡ የሳር ክዳን ባላቸው ትናንሽ ጎጆዎች ተጨናንቆ ነበር። ዕይታው ቤታቸውን በውኃ ዳርቻ የገነቡ ነዋሪዎች ያላትን የኢጣልያ ከተማ የሆነችውን ቬኒስን የሚያስታውስ ነበር። ስፓንኛ ተናጋሪ የሆኑት አሳሾች ቦታዋን “ትንሿ ቬኒስ” የሚል ትርጉም የያዘውን ቬነዙዌላ የሚለውን ስያሜ ሰጧት።
ዛሬ በዚህች ውብ አገር ውስጥ ለየት ያለ የግንባታ ፕሮግራም በመካሄድ ላይ ነው፤ መንፈሳዊ የግንባታ ፕሮግራም። በዚህች አገር የይሖዋ ምሥክሮች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የመንግሥቱን ዘር በመዝራት ላይ ናቸው። የዚህ ውጤት የሆነው መንፈሳዊው መከር “የመከሩ ጌታ” ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ከፍተኛ ውዳሴ እያስገኘለት ነው።—ማቴዎስ 9:37, 38
አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች በሰሜን ምዕራብ ቬነዙዌላ በምትገኘው የሱሊያ ግዛት ውስጥ የሚገኝ አንድ ጉባኤ በጎበኘበት ወቅት በአካባቢው ያሉት ምሥክሮች እሱና ሚስቱ በአቅራቢያው ያለችውን ቶአስ የምትባል አንድ ትንሽ ደሴት እንዲጎበኙ ዝግጅት አደረጉ። በማለዳ ወደ ደሴቲቱ በሚሄደው ጀልባ ላይ ለመሳፈር በሰልፍ እየጠበቁ ሳለ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሚስት የሆነችው ሜሪ የሙሉ ጊዜ አቅኚ ለሆነችው የአገልግሎት ጓደኛዋ ጀልባው ላይ ያሉትን አንዳንድ ሠራተኞች ለማነጋገር ሐሳብ አቀረበችላት። አቅኚዋ እኅትም በነገሩ ተስማማች።
ሜሪ ወደ አንዱ መካኒክ ጠጋ አለችና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ አስተዋወቀችው። “አምላክን የሚያስከብር ቤተሰብ መመሥረት” የሚለውን ምዕራፍ ስታሳየው ጉዳዩ ጠቃሚ መሆኑን ተገነዘበ። በመቀጠልም ሜሪ በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት እቤቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊደረግለት እንደሚችል ገለጸችለት። መጽሐፉን የወሰደ ሲሆን አንድ ሰው ቤቱ ሄዶ እንዲያነጋግረውም ዝግጅት ተደረገ።
ከትንሽ ጊዜ በኋላ በዚያ አካባቢ ለአንድ ቀን የሚደረግ ልዩ ስብሰባ ነበር። መካኒኩ ሲኞር ናቫ ከሚስቱና ከሁለት ሴት ልጆቹ ጋር ስብሰባው ላይ ተገኝቶ ስታይ ያልጠበቀችው ስለነበረ በጣም ተደሰተች። ሜሪ ቤተሰባቸው ስለሚያደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ምን አመለካከት እንዳላት ሚስትየውን ጠየቀቻት። የሰጠችው መልስ እጅግ አስገራሚ ነበር።
“እውነትን በማወቃችን ይሖዋን አመሰግነዋለሁ” ስትል መለሰችላት። ቀጥላም እንዲህ ስትል ገልጻለች:- “ባለቤቴን ያነጋገራችሁት ሌላ ሴት ወድዶ ትቶኝ በሄደበት ጊዜ ነበር። ከባድ ጠጪም ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሲሰክር ይሳደባል፤ ይህ ደግሞ በደሴቲቱ ላይ ያለውን ጥቂት ነዋሪ ያስከፋ ነበር። በመናፍስታዊ ሥራዎች ይካፈል ነበር። ይሁን እንጂ በጥናቱ አማካኝነት ያገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በሕይወቱ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ እንዲያደርግ ረድቶታል። መጥፎ ልማዶቹን በሙሉ ትቷል። ካቶሊክ የሆኑት ወላጆቹ ባደረገው ለውጥ በጣም ተደንቀዋል። ባሁኑ ጊዜ ኃላፊነት የሚሰማው ባልና አባት በመሆኑ ተደስተዋል።”
ሲኞር ናቫ በ1996 የተጠመቀ ሲሆን አሁን የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነው። ባለቤቱ ጄኒ በ1997 ተጠምቃለች። የከተማው ከንቲባ ይህ የጀልባ መካኒክ ባደረገው ለውጥ በጣም ከመደነቃቸው የተነሳ እሳቸውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። እነዚያ እህቶች በዚያች ዕለት ጠዋት ጀልባዋን እየጠበቁ ሳሉ ምሥራቹን ከማወጅ ወደ ኋላ ባለማለታቸው ምንኛ ተደስተዋል!
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ምሥራቹን ለአንድ የጀልባ መካኒክ ማካፈሉ አስደሳች ውጤት አስገኝቷል